ቀጥታ፡

1 ሺህ 440ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል በመላው ሀገሪቷ እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ ግንቦት 27/2011 ፡ 1 ሺህ 440ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል ዛሬ በመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በመከበር ላይ ይገኛል።

በዓሉ ከማለዳው ጀምሮ ህዝበ ሙስሊሙ(ጀምዐ) በተገኘበት በሶላትና በስግደት ነው እየተከበረ ያለው።

በተለይም በአዲስ አበባ ስታዲየም የእምነቱ ተከታዮች፣ የፌዴራልና የከተማው አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት እየተከበረ ይገኛል።

በበዓሉ ላይም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቀዳሚ ሙፈቲ ሃጂ ኡመር እንድሪስ እና የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተገኝተዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ-አልፈጥር በዓልን በጋራ ተሰባስቦ በመስገድ፣ በመተሳሰብና በመተዛዘን እንድያከብርም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቀዳሚ ሙፈቲ ሃጂ ኡመር እንድሪስ በትናንትናው እለት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።.

ቀዳሚ ሙፈቲ ሃጂ ኡመር እንድሪስ በዚሁ መልዕክታቸው ህዝበ ሙስሊሙ በእለተ በዓሉ ተሰባስቦ የኢድ ሶላት ከሰገደ በኋላ በመጠያየቅ፣ ያላቸው ለሌላቸው በመስጠት አብሮነታቸውን እንድያሳዩም አሳስበዋል።

በዓሉ በሰላም፣ በመተዛዘንና በጋራ በመደሰት በተክቢራ (ፈጣሪን በማወደስ) እንደሚከበርም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ የተለያዩ አካላትም በዓሉን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም