ቀጥታ፡

ችግኝ ተከላ እንደ አንድ የሃይማኖት አስተምህሮ ሊተገበር ይገባል ተባለ

ግንቦት 26/2011 በአገሪቷ የደን መመናመንና በረሃማነት የፈጠረውን ስጋት ለመከላከል ችግኞችን ማልማትና መንከባከብ ምእመኑም ሆነ ማህበረሰቡ እንደ አንድ የሃይማኖት አስተምህሮ ሊተገብረው ይገባል ሲሉ የተለያዩ የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ።  

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የመገናኛ ብዙሃን ስራ አስኪያጅ መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል ”የሃይማኖት ተቋማት ከሃይማኖት አስተምህሮ ባሻገር በመፅሃፍ ቅዱስ ተጠቅሶ እንደምናገኘው ፈጣሪ የሰው ልጅ ሲፈጥረው በምድር ያሉ ስነ-ፍጥረታት ተንከባክቦ በአግባቡ እንዲጠቀምበት ነው” ይላሉ፡፡

የአብያተ ክርስቲያናት ግንባታ ሲታሰብ ዓፀደ ቤተ-ክርስተያን አብሮ ስለሚታሰብ በገጠርም ሆነ በከተማ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት የተሻለ የደን ይዞታ እንዲኖር ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክቷል በማለትም ይገልጻሉ፡፡

“በቤተክርስቲያን መዋቅር ውስጥ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የሚባል ትልቅ ኮሚሽን አለ፤ በኢትዮጵያ ብቸኛ ከ40 አመት በላይ ደንን በማልማት የተቀመጠ ነው። አንዱ ዘርፍ ደን ያለማል ሌላው ቦሌ አካባቢ በአንድ ገዳም ውስጥ ችግኝ በማፍላት ለሕብረተሰቡ ይሰጣል፡፡ይህ እንቅስቃሴ ጊዜና አዋጅ ጠብቆ ሳይሆን በቋሚነት የሚከናወን ስራ ነው’’ በማለትም ለአብነት አንስተዋል።  

በቤተ ክርስቲያን መመሪያ ተሰጥቶት በኮሚሽኑ ውስጥ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ መምርያ ተዋቅሮሥራውን እያከናወነ እንደሆነ የገለጹት መምህር ዳንኤል፤ መምሪያው ከምእመኑ ጋር ሆኖ ከመንግስት ቦታ በመጠየቅ ለአገር በቀል ዛፎች ቅድሚያ በመስጠት በየጊዜው የችግኝ ተከላ ስራ እንደሚከናወንም ነው የጠቀሱት።  

ቤተ-ክርስቲያኗ በመንግስት በኩል የቀረበውን የችግኝ ተከላ ፕሮግራም የምትደግፈውና የያዘችውን ፕሮግራም የሚያበረታታ በመሆኑ ሥራው ተጠናክሮ  እንድቀጥል ያግዛል ብለዋል፡፡

በየጊዜው የሚደረገው የችግኝ ተከላ ዘመቻ እና እንክብካቤ ከመንግስት ይልቅ የሃይማኖት አባቶች ሃላፊነት ነው ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነ እየሱስ ቤተ-ክርስትያን በወንጌልና ስነ-መለኮት መምሪያ ውስጥ የዲያቆን ቢሮ ሃላፊ ቄስ ፀጋነሽ አያሌው ናቸው።

“በመፅሃፍ ቅዱስ እንደተቀመጠው እግዚአብሄር የሰው ልጆች ሲፈጥራቸው ምድርንና ፍጥረቶቿን ጠብቃቹና ተንከባክባችሁ ተጠቀሙ ብሏልና እኛ የሃይማኖት መሪዎች ደግሞ ይህንን የማስፈፀም ግዴታ አለብን” ነው ያሉት።

ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰዎች በግንዛቤ እጥረት ምክንያት ስለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ቸልተኛ እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቅሰው፤ የሃይማኖት መሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጥ ግዴታና ሃላፊነት በተገቢ ሁኔታ እየተወጡ እንዳልሆነም ገልፀዋል፡፡

መንግስት በትምህርት ካሪኩለሙ የደን ልማት አስፈላጊነትን ለወጣቱ ትውልድ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሚሞክረው ሁሉ የሃይማኖት መሪዎችም ተፈጥሮን ከመፅሃፍ ቅዱስ በማጣጣም በአስተምህሯቸው የድርሻቸው ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ከአሁን በፊት በየአመቱ የእምነቱ ተከታይ ተማሪዎች ለእረፍት ከተለያየዩ ዩኒቨርስቲዎች ሲመጡ አቅመ ደካሞችን ከመርዳትና ከማገዝ ባሻገር የችግኝ ተከላ ላይ እንዲሳተፉ እናደርጋለንም  ነው ያሉት፡፡

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሃጂ አብዱልአዚዝ ወጉ በበኩላቸው የአካባቢ ጥበቃን በተመለከተ ሃይማኖቱ ራሱን የቻለ አስተምህሮ እንዳለው ጠቅሰው፤ ችግኝ ተክሎ ከመንከባከብ ባሻገር እጽዋት ያለአግባብ መቁረጥን እንደሚያወግዝ  ገልፀዋል፡፡

አብዛኞቹ በአዲስ አበባና ዙርያዋ የሚገኙ መስጊዶች ጠባብ በመሆናቸው ከአምልኮ ስራ ባለፈ ችግኝ ለመትከል የሚያስችል ትርፍ ቦታ የላቸውም ያሉት ሃጂ አብዱልአዚዝ፤ ሰፋ ያለ ቦታ ያላቸው መስጊዶች ላይ ግን የአረንጓዴ ልማት ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡  

የደን መመናመንና በረሃማነት የፈጠረውን ስጋት ለመከላከል የእምነት መሪዎች ችግኞችን ከመትከል ባሻገር መንከባከብና የተተከሉትን ባለመቁረጥ ለምእመኑም ሆነ ለአጠቃላይ ማህበረሰቡ የግንዛቤ ስራ መሰራት እንዳለበት መክረዋል፡፡

’’በህብረተሰቡ ዙርያ የሚተከሉ ችግኞች ከውበት መስህብነታቸው ባሻገር በህይወት የመኖራችንም ሚስጥር ናቸውና እንደ አንድ የሃይማኖት አምልኮት ተግባር ወስደን ልንከባከባቸው ይገባል’’  በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም