ቀጥታ፡

ማህበረሰቡና መንግሥት ከስነ ምግባር ውጪ የሆኑ ተግባራትን በቸልታ መመልከት የለባቸውም

ግንቦታ 26/2011  በኢትዮጵያ ከስነ ምግባር ውጭ የሚፈጸሙ ድርጊቶች እየተስፋፉ መምጣት እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስታወቀ። 

በአገሪቷ አሁን አሁን ከስነ ምግባር ወጪ የሆኑ ተግባራት እየተስፋፉ መምጣታቸው  በቸልታ  ሊታይ  እንደማይገባ ነው ተቋሙ ያሳሰበው።   

የጉባኤው ዋና ጸሀፊ ሊቀ-ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ከስነ ምግባር  ውጭ  የሆኑ ባእድ ድርጊቶች በተለይም ግብረ ሰዶማዊነት በየትኛውም ኃይማኖትም ሆነ በአገሪቷ ሕግ ተቀባይነት የለውም።   

በመሆኑም ''የግብረ ገብና የስነ ምግባር ልዕልና ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያ በኢ-ስነ ምግባራዊና ኢ-ግብረገባዊነት ድርጊት እንድትታማ ከቶም መፍቀድ የለብን'' ነው ያሉት። 

የኃይማኖት ተቋማት ትውልዱን በስነ-ምግባር እሴቶች ሲያንጹ መቆየታቸውን  አስታውሰው አሁንም  ይህንን ተግባራቸውን  እንዲያጠናክሩም ጥሪ አቅርበዋል።    

በአገሪቷ ወቅታዊ ስጋት እየሆኑ ከመጡ ጉዳዮች መካከል ግብረ ሶደማዊነት አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ጸሀፊው ድርጊቱ በኃይማኖቶች ሀጥያት ፣በባህል ጽዩፍና በአገሪቷ ሕግም ወንጀል ነው ብለዋል።  

እንደ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገለጻ ዓለም የደሰረበት ቴክኖሎጂ ሰዎችን እርስ በእርስ የማገናኘትና ኑሮን የማቅለል ሚና ቢኖረውም በሌላ በኩል የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት እንዲስፋፋ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑ ከግምት ሊገባ ይገባል።    

የግብረ ሰዶም አስተሳሰብ በማህበራዊ የትስስር ገጽ በስፋት እየተቀነቀነበት መሆኑን ገልጸው ''አስተሳሰቡ በአገራችን እያቆጠቆጠና ተከታዮችም እያፈራ ይገኛል፤ የአስተሳሰቡ  አራማጆች  ወንጀሉን  ከሰብአዊ መብት  ጋር በማያያዝ ቅቡል እንዲሆን ለማድረግ እየሰሩ ነው'' ሲሉም አመልክተዋል።   

ዋና ጸሀፊው እንደሚሉት አገራትና ድርጅቶች ብቁና አምራች ዜጋን ለዚህ እኩይ ተግባር በመመልመል ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙም እሙን ነው። በመሆኑም ሁሉም ኃይማኖቶችና አማንያን በአንድ ላይ አቋም በመያዝ ትውልዱን መታደግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።  

መንግሥትም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም