ቀጥታ፡

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሰላም ዋንጫን ተረከበ

ግንቦታ 26/2011 የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሰላም ዋንጫን ከመከላከያ ሰራዊት ተረከበ። 

የሰላም ዋንጫው ከየካቲት ወር 2010 ዓ.ም ጀምሮ በመከላከያ ሰራዊት ዕዞች ውስጥ ሲዘዋወር ቆይቷል።

የህዳሴ ግድብ የሰላም ዋንጫ በየተቋማት እየተዟዟረ ያለው ግድቡ ለልማት ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ በተጨማሪ የሰላም ምንጭ መሆኑን ለማስገንዘብና ገቢ ለማሰባሰብ በሚል ዓላማ ነው።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ዛሬ የሰላም ዋንጫውን በኮልፌ (በቀድሞ ስሙ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ካምፕ) በሚገኘው የኮሚሽኑ የፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፕ በተከናወነ ስነ-ስርአት ተረክቧል።

ዋንጫውን  ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል እንደሻው ጣሰው ያስረከቡት የኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት የኢንዶክትሪኔሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል መሐመድ ተሰማ  ናቸው።

ኮሚሽነር ጀነራል እንደሻው ጣሰው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ኮሚሽኑ የህዳሴ ግድቡ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ ለግንባታው ስኬት የተለያዩ  ድጋፎችን እያከናወነ ይገኛል።

 የፌደራል ፖሊስ አባላት ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ለግድቡ ደህንነት ያልተቋረጠ ጥበቃ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ለግድቡ ከሚደረገው ጥበቃ በተጨማሪ የኮሚሽኑ ከፍተኛ አመራሮች እና አባላት በሙሉ ፈቃደኝነት ከደመወዛቸው ላይ እየተቆረጠ ከ248 ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዢ በመፈጸም አገራዊ የዜግነት አሻራቸውን ማሳረፋቸውን ገልጸዋል።

የህዳሴ ግድብ የሰላም ዋንጫ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ስር በሚኖረው ቆይታ በኮሚሽኑ አራት የስራ ክፍሎች የታላቁ የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ የንቅናቄና የቅስቀሳ ስራዎችን በማድረግ የገቢ ማሰባሰብ ተግባር የሚከናወን መሆኑንም አመልከተዋል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ የሚያስፈልገውን ማንኛውም ድጋፍ እንደሚያደርግም ኮሚሽነር ጀነራል እንደሻው ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት የኢንዶክትሪኔሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል መሐመድ ተሰማ በበኩላቸው የህዳሴው ግድብ ግንባታ መከናወን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት እስከ አንድ ቢሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የመከላከያ ሰራዊት የህዳሴው ግድብ ሥራ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ይካሄድ ዘንድ አስፈላጊውን  የጥበቃና የደህንነት ስራ እያከናወነ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

ግንባታው እንዲጠናቀቅ ሰራዊቱ የሚያደርገውን ድጋፍና ተሳትፎ እጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሜጀር ጀነራል መሐመድ አረጋግጠዋል።

የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የሚዲያ ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ለ15 ወራት ገደማ የሰላም ዋንጫው በመከላከያ ሰራዊቱ በነበረው ቆይታ ከ197 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ገልጸዋል።

በርክክብ ስነ ስርአቱ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት እና የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የስራ ሃላፊዎችና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጋቢት 24 ቀን 2004 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ መጣሉ የሚታወስ ነው።

በስምንት ዓመት የግድቡ ግንባታ አጠቃላይ የሲቪል ሥራዎች አፈፃፀም 83 በመቶ፤ የኤሌክትሮ መካኒክ ሥራዎች 25 በመቶ፤ ሀይድሮሊክ ስቲል ስትራክቸር 13 በመቶ ሲሆን በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ አማካይ አፈፃፀሙ 66 በመቶ ደርሷል።

የግድቡ ግንባታ ሲጀመር 80 ቢሊዮን ብር ይፈጃል ተብሎ የተያዘ ቢሆንም አሁን 98 ነጥብ 7 የገንዘብ ክፍያ አፈፃፀም አለው፤ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ በአጠቃላይ 150 ቢሊዮን ብር ይፈጃል ተብሎም ይጠበቃል።

አሁን በተደረገው የለውጥ እርምጃ በታህሳስ ወር 2013 ዓም የግድቡ ሁለት ተርባይኖችን በመጠቀም ኃይል ማመንጨት ይጀምራል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም