የፖለቲካ ፓርቲዎች ህዝብን በስሜት መምራታቸው ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እንዳይዳብር አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የፖለቲካ ፓርቲዎች ህዝብን በስሜት መምራታቸው ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እንዳይዳብር አድርጓል
ግንቦት 26/2011 በሀገሪቱ ያሉ አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከእውቀት ይልቅ ህዝብን በስሜት በመምራታቸው ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እንዳይዳብር ማድረጉን የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አንድ ምሁር ተናገሩ።
በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ጌታቸው ፋንታሁን፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ተሳታፊ በመሆን ርእዮተ አለማቸውን በማስተዋወቅ ለህዝብ ጥቅም አማራጭ መፍትሄ በማቅረብ መንግስትን በምክንያት መሞገት ቀዳሚ አጀንዳቸው ነው ይላሉ።
አላማውን ከግብ ለማድረስ የፖለቲካ ምህደር መስፋትን፣ የህዝብ ተሳትፎ ማደግን፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ገለልተኛነትና አሳታፊነትን እንደሚጠይቅ አስረድተዋል፡፡
የህብረተሰቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች ለመለየት የተዋረድ መዋቅር መዘርጋት ለፖለቲካ ፓርቲዎች አስገዳጅ ነው ያሉት መምህር ጌታቸው“ በሀገራችን መድብለ ፓርቲ አለ ቢባልም በተለያዩ መክንያቶች ከስም በዘለለ ርእዮተ አለማቸውን ለህዝብ በማስተዋወቅ መንግስት የሚመሰርቱበትን አቅም መፍጠር አልቻሉም” ብለዋል፡፡
የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ያለ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ እውን እንደማይሆን የገለጹት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ፤ ላለፉት አመታት ከዚህ በተቃርኖ በመሰራቱ ዜጎችን የማህበራዊ ፍትህ ማሳጣቱን ተናግረዋል።
በሀገሪቱ ቀደም ሲል በፓርቲዎች የሚታይ ከላይ ያለ አመራር “ሲፈለግ ወደ ታች ሀሳብ የሚያወርድበትና የሚሰነጥቅበትን” የሀግ ስልጣን በማስቀረት ለታችኛው መዋቅር መሰጠቱንም ተናግረዋል፡፡
በዘመናዊ አስተዳደር ውስጥ በሀሳብ የተደራጀ ሀይል ሀገርን በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንደሚመራ የተናገሩት የአንድነት ለዴሞክራሲ ና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀ መንበር አቶ ትግስቱ አወሎ፤ በዚህ ሂደትም አሸናፊነት የሚወሰነው በህዝብ ድምጽ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
“ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ ሰርተፊኬት ከመያዝ ውጭ ያደረጉት ነገር የለም” ያሉት የፓርቲው ሊቀመንበር ለዚህ እንደ ምክንያት የሚያነሱት የገዢው ፖርቲ ጫና፣ ነጻ ሚዲያ አለመኖሩን ና የውስጠ ዴሞክራሲ እጦትን ነው፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠበቅባቸውን መፈጸም ያለመቻላቸው የህብረተሰቡ ፖለቲካዊ ንቃተ ህሊና እምብዛም ያለመሆን፣ የዴሞክራሲ ስርአት አለመዳበሩ ና የሚዲያ ነጻነት አለመኖሩን በምክንያት የሚጠቅሱት ደግም መምህር ጌታቸው ናቸው ፡፡
በአሁኑ ሰአት በየአካባቢው የጸጥታ ስጋት መኖሩ ፓርቲዎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው አባላት እንዳያፈሩ ማድረጉን የተናገሩት መምህሩ፤ በግለሰብና በፓርቲዎች መካከል የሚፈጠሩ ሽኩቻም የህብተሰቡን የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ተሳትፎ ጎድቶታል ይላሉ፡፡
“የተቃውሞ ጎራው እርስ በርስ የሚፈራረጅና ለፖለቲካ ስርአት ግንባታ ሳይሆን የግለሰብ አስተሳሰብ ማእከል በማድረግ መንቀሳቀሱ ህዝቡን ለዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ አዘጋጅተነዋል ማለት አይቻልም’’ ያሉት ደግሞ አቶ ትግስቱ ናቸው፡፡
አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከእውቀት ይልቅ ህዝብን በስሜት መምራታቸው “ያሳለፍነው ዘመን በጥላቻና በንትርክ ስለሆነ ገዢው ፓርቲ ያንበሳውን ድርሻ ቢወስድም የኛም አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል አይደለም” ሲሉ አቶ ትግስቱ ይገልጻሉ፡፡
“የተሻለ አስተሳሰብ አለኝ የሚል አካል ራሱን አጥሮ ሊመረጥ አይችልም ” የሚሉት አቶ ዋሲሁን፤ ሀሳብን ለህዝብ በመግልጽና መድረኩን ክፍት በማድረግ መወዳዳር የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አቋም እንዲሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም ተናግረዋል።
“በብሄርም ሆነ ብሄራዊነት” የሚደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተነሱበት ህዝባዊ መሰረት እንደተጠበቀ ሆኖ በሚያግባቡ ሀገራዊ እሴቶች ላይ መስራት እንዳለባቸው የሚመክሩት መምህር ጌታቸው፤ አማራጭ ሀሳብ ማቅረብ ሳይቻልና ግለሰባዊ ጥፋቶችን ለመሸፈን ብሄርን መሸሸጊያ ማድረግ እንደማይገባም አስረድተዋል፡፡