ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ አለም አቀፍ ኮንፈረንስ ላይ ለመሳተፍ ቫንኮቨር ካናዳ ገብተዋል

80

ግንቦት 26/2011 ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በስርዐተ ጾታ እኩልነት ፣በጤና እና በመብት ጉዳዮች ላይ በሚመክረው አለም አቀፍ ኮንፈረንስ ላይ ለመሳተፍ ቫንኮቨር ካናዳ ገብተዋል።

የካናዳ መንግስት የስራ ሀላፊዎች ፣በካናዳ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች እና በካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አቀባበል አድርገውላቸዋል። 


የውመን ዴሊቨር 2019 ኮንፈረንስ ከግለሰብ እስከ ቡድን ድረስ ያለውን አቅም በመጠቀም የስርዐተ ጾታ እኩልነት የነገሰበት አለም ለመፍጠር በሚቻልበት ዕድል ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ፕሬዝዳንቷ በዚያ ከሚኖሩ  ኢትዮጵያውያን ጋር ተገናኝተው ባስተላለፉት መልእክት  "አንድነታችንን አጠናክረን ኢትዮጵያን ለመገንባት ቆርጠን መነሳት አለብን “ብለዋል።

“ሁላችንም አንድ ሆነን ብቸኛዋን ሀገራችንን ለማሳደግ ከመስራት ውጭ አማራጭ የለንምና እናንተም የምትችሉትን ሁሉ ለኢትዮጵያ አድርጉ።" ብለዋል በመልዕክታቸው።

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተወካዮቻቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት  "የሀገራችን መሪ ከሀምሳ አመት በኋላ ወደ ቫንኮቨር ሲመጡ ፕሬዝደንቷ የመጀመሪያዋ በመሆናቸው ከፍተኛ ደስታ ፈጥሮብናል”ብለዋል፡፡

 መንግስት ለሚያደርግላቸው ኢትዮጵያን የማልማት ጥሪ የሚችሉትን ሁሉ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን መግለፃቸውን ከፕሬዝዳንቷ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም