የከተማዋን የቤት ችግር ለመፍታት የአገር በቀል የቤት አልሚዎች ተሳትፎ ወሳኝ ነው

71

አዲስ አበባ  ግንቦት 25/2011መንግስት የከተማዋን የቤት ችግር ለመፍታት ለሚያደርገው እንቅስቃሴ የአገር በቀል የቤት አልሚዎች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገለጸ።

ኖህ ሪል ስቴት ከሚያስገነባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ በዛሬው እለት 200 ዎቹን ለባለቤቶቹ  አስተላልፏል።

የአስተዳደሩ የኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ህላዌ ሰውነት በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በከተማዋ የቤት ፍላጎትና አቅርቦትን ችግር ለመፍታት ታማኝና የህዝብ ገንዘብ ተቀብለው በአግባቡ የሚጠቀሙ ቤት ገንቢ ተቋማት ያስፈልጋሉ።

ይህም መንግስት የቤት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ከግሉ ሴክተር ጋር መስራት ያሰበውን ስራ የተሳካ ያደርገዋል ብለዋል።

ኖህ ሪል ስቴት ቤቶቹን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ገንብቶ ለባለቤቶቹ ማስተላለፍ መቻሉ የህዝብ አመኔታ ማግኘት ብቻ ሳይሆን የከተማዋን ገጽታም ከፍ ለማድረግ የራሱን አስተዋጾኦ ለማበርከት እንዳስቻለው ተናግረዋል።

ቤት ከመጠለያ ባሻገር የማህበራዊ መስተጋብር ዋነኛ ሃብት መሆኑን የጠቀሱት ምክትል የቢሮ ኃላፊው፤ የከተማ አስተዳደሩ የቤት ችግርን ለመፍታት ከአገር በቀል የቤት አልሚዎች ጋር ይሰራል ብለዋል።

የኖህ ሪል ስቴት ማኔጅመንት አባል አቶ ዐቢይ ኃይለማርያም በበኩላቸው መንግስት ከሚሰራው የቤት ልማት ፕሮጀክት በተጓዳኝ የግሉ ሴክተር ተሳትፎ ወሳኝ ነው።

ለዚህም ማህበሩ በርካታ የቤት ልማት ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን በቀጣይም መካከለኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ከ10 እስከ 15 በመቶ ቅድመ ክፍያ በመክፈልና ቀሪውን በረዥም ጊዜ በመክፈል የቤት ባለቤት እንዲሆኑ የሚያደርግ ስራ ለመስራት ማቀዳቸውን ጠቁመዋል።

ለቢሮና ለንግድ የሚሆኑ ህንጻዎችንም በመገንባት በአነስተኛ ዋጋ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር ለመከተል እየተሰራ እንደሆነ አቶ አቢይ ተናግረው፤ ይህም በቢሮና በንግድ ቤት ኪራይ ላይ የሚታየውን የዋጋ ንረት ለማስቀረት ያግዛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም