ቀጥታ፡

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ

አዲስ አበባ ግንቦት 25/2011 በሶማሊያው ፕሬዝዳንት መሀመድ አብዱላሂ መሀመድ የሚመራ ልኡካን ቡድን ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ዛሬ አዲስ አበባ ገብቷል። 

ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች  በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ተገኝተው  ለሶማሊያው ፕሬዝዳንትና ልዑካን ቡድናቸው አቀባበል አድርገዋል።

ፕሬዝዳንት መሓመድ አብዱላሂ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድና ከሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ይኖራቸዋል።

የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት ዶክተር አብይ አህመድ  የአፍሪካ ቀንድን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ እንደዚሁም የኢኮኖሚያዊ ውህደትን ለማምጣት  እየሰሩዋቸው ያሉ ስራዎችን ለማጠናከር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ ፕሬዝዳንት መሓመድ አብዱላሂ በጉብኝታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጋር የአገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነትና የቀጠናውን ትብብር ለማጠናከር በሚያሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም