ቀጥታ፡

ብዝሃ-ህይወትን በመጠበቅ የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል ይገባል…የኢትዮጵያ ብዝኀ ሕይወት ኢንስቲትዩት

ግንቦት 24/2011 በብዝሃ ሕይወት ሀብት ላይ እየደረሰ የሚገኘውን አደጋ በመከላከል የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖን ለመከላከል ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ብዝኀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ጥሪ አቀረበ።

በኢንስቲትዩቱ የጎባ መዕከል 18ኛውን ዓለም አቀፍ የብዝሃ ህይዎት ቀን በዞን ደረጃ ’’ብዝሃ ህይዎታችን ምግባችን ጤናችን ’’ በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ መርሃ-ግብሮች በባሌ ጎባ ተከብሯል፡፡

በበዓሉ ላይ የተገኙት በኢንስቲትዩቱ የጎባ ብዘኀ ህይወት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ግርማ እንደተናገሩት ኢንስቲትዩቱ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸውን ሀገር በቀል የእንስሳትና እፅዋት ዝርያዎች ለመታደግ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት  እየሰራ ነው፡፡

“የበዓሉ መከበርም ቀጣይነት ያለው ብዝሀ ህይዎት እንዲኖር ከማድረግም ባሻገር የአካባቢው ማኅበረሰብ ስለብዝኀ ሕይወ ያለው ግንዛቤ እንዲጨምር ያደርጋል”ብለዋል፡፡

“በተለይ በትምህርት ቤቶች መከበሩ አዲሱ ትውልድ የብዘኀ ሕይወት ሀብትን መጠበቅና በዘላቂነት መጠቀም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ  ግንዛቤ  እንዲኖራቸው  ያስችላል”  ብለዋል፡፡

በብዝኀ ሕይወት ዙሪያ በሁሉም ሕብረተሰብ ዘንድ ግንዛቤ መፈጠሩ አሉታዊ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስና ለስነ-ምህዳር ፈታኝ  የሆነውን  መጤ ዝርያ  ለመግታት  አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል።

ማዕከሉ የብዘኀ ህይወት ሀብት ተጠብቆ በዘላቂነት ጥቅም ላይ እንዲውል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ከመስራት በተጓዳኝ በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በጥናት ለመለየት በአካባቢው ከሚገኙ የምርምርና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ማዕከሉ በሀገር ደረጃ የታያዘውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን ከግብ ለማድረስ በየዓመቱ ከ70ሺህ የሚበልጡ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያላቸው ሀገር በቀል ችግኞችን ለተለያዩ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች ተቋማት በማሰራጨት መተከላቸውን ጠቁመው ባለፉት ዓመታት የተተከሉት 800ሺህ የሚበልጡ ሀገር በቀል ችግኞች በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

ይህንኑ የብዝሃ ህይወት ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል በሚደረገው ርብርብ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡም ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል ።

ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል የኡርጂ በሪሳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተፈጥሮ ሀብት ክለብ መምህር አለማየሁ ስሳይ በሰጡት አስተያየት ትምህርት ቤቱ ተማሪዎችን በብዘኀ ህይወት ክለብ በማደራጀት ከራሳቸው አልፈው ለማህበረሰብ ግንዛቤ እንዲፈጥሩ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

“በዓሉ በትምህርት ቤቶች መከበሩ ወጣቱ ትውልድ ስለብዘኀ ህይወት ግንዛቤ ኖሮት በጥበቃውም ላይ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ያስችላል” ብለዋል፡፡

ሌላው የበዓሉ ተሳታፊ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ፍሬዘር ጎሳ በበኩሉ “ በትምህርት ቤታቸው በብዝሃ ህይወት ክለብ በመሳተፍ  የቀሰመው እውቀት ግንዛቤውን እያሳደገ እንዲመጣ እንዳገዘው ተናግሯል፡፡

በበዓሉ ላይ ከትምህርት ቤቶቹ ማህበረሰብ ባሻገር የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን በመርሃ ግብሩ ላይ ከብዘሃ ህይወት ጋር የተገናኘ  ድራማ፣  የጥያቄና  መልስ  ውድድርን ጨምሮ የችግኝ ተከላ ተካሄዷል፡፡

የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት እ.ኤ.አ በ1976 በኢትዮጵያና በጀርመን መንግስት መካከል በተደረገ ስምምነት መሰረት የዕፅዋት ጀነቲክ ሀብት በሚል ስያሜ ለመጀመሪያ ጊዜ መቋቋሙን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም