ለግብርና እድገት የዘርፉ ተመራማሪዎች ቴክኖሎጂን የማስፋፋት ኃላፊነት አለባቸው….ግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ለግብርና እድገት የዘርፉ ተመራማሪዎች ቴክኖሎጂን የማስፋፋት ኃላፊነት አለባቸው….ግብርና ሚኒስቴር
ግንቦት 24/2011 ኢኮኖሚው ዘርፍ ግብርናው የመሪነት ሚናውን እንዲጫወት በቴክኖሎጂ የማስደገፍና የተሻሻሉ ዝርያዎችን የማስፋፋት ኃላፊነት የዘርፉ ተመራማሪዎች መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የትግራይ ልማት ማህበር በእስራኤል አገር ከሚገኝና ካልቲቭ ኤይድ ከተባለ አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር ያቋቋሙትን ቀላሚኖ የግብርና ኢንቨስትመንት ማዕከል እንቅስቃሴ በግብርና ሥራ በተሰማሩ ባለሀብቶችና በዘርፉ ተመራማሪዎች ተጎብኝቷል።
በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እያሱ አብረሀ እንዳሉት በማዕከሉ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሀብቶችና ለተመራማሪዎች የይቻላል መንፈስን እንዲሰንቁ የሚያበረታታ ነው።
የግብርና ስራውን ለማዘመን የሚያግዙ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በማዕከሉ የመስክ ምልከታ ላይ ማየታቸውን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በተለይ የጠብታ መስኖ የግብርና ቴክኖሎጂ በውስን መሬትና ውሃ የተሻለ ምርት ማግኘት እንደሚቻል በተጨባጭ ማየታቸውን ተናግረዋል።
በሀገሪቱ ግብርናው የመሪነት ሚናውን እንዲይዘም የዘርፉ ተመራማሪዎች ግብርናውን በቴክኖሎጂ የማስደገፍና የተሻሻሉ ዝርያዎችን ወደ አርሶ አደሩ በማስፋፋት ተጠቃሚ የማድረግ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
“የተለያዩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በመስኖ የሚመረተው በገበያ ተፈላጊና፣ ጥራቱን የጠበቀና ብዛት ያለው እንዲሆን በትኩረት መስራት ያስፈልጋል” ብለዋል ዶክተር እያሱ።
በጉብኝቱ ላይ የተገኙት በትግራይ ልማት ማህበር ካልቲቭ ኤይድ ተወካይ ሚስተር ቶመር ማልቺ ለተክል የሚሆን ቀዳዳ በማስቀረት አፈሩን በፕላስቲክ መሸፈን ተክሉ በቂ ሙቀት አግኝቶ በፍጥነት ለምርት እንዲደርስ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂው በተክሉ ስር ያለው እርጥበት በፀሐይ ትነት እንዳይሄድ ፕላስቲኩ እንዲከላከል የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ተክሉን የሚጎዱ የተለያዩ ተባዮች ሙቀት የሚይዘው ፕላስቲክ ላይ ሲያርፉ በቀላሉ እንዲያቃጥላቸው የሚያደርግ መሆኑንም አስረድተዋል።
እንደ ሚስተር ቶመር ገለጻ ቴክኖሎጂውን ምርትን ከሦስት እጥፍ በላይ ለማሳደግ የሚያስችል ሲሆን ብዙ ወጪና ጉልበት የማይጠይቅ ነው።
የትግራይ ልማት ማህበር ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታደለ ሐጎስ በበኩላቸው የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በክልሉ ለማስፋፋት የተፈለገው የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በማልማት በክልሉ የሚታየውን የመቀንጨር ችግር ለመከላከል ነው።
“በማዕከሉ በቴክኖሎጂ በመታገዝ በአነስተኛ መሬትና በጥቂት ውሃ ብዙ ማምረት እንደሚቻል ማየት ተችሏል” ያሉት ዶክተር ታደሰ፣ ልማት ማህበሩ የማዕከሉን ተሞክሮ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የማስፋፋት ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል።
ከመስክ ጉብኝት ተሳታፊዎች መካከል ከመቀሌ እርሻ ምርምር የመጡት ዶክተር በረከት ኃይለስላሴ ከጉብኝቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት ከውሃ አጠቃቀም ጀምሮ ቴክኖሎጂዎቹ በአገራችን ሊተገበሩ የሚችሉና የተሻለ ምርት ለማግኘት የሚረዱ መሆናቸው ተናግረዋል።
በግብርና ዘርፍ የተሰማሩት ባለሀብት አቶ ዳዊት ኃይለስላሴ በበኩላቸው በጉብኝቱ ከአዳዲሶቹ የግብርና ቴክኖሎጂዎች በተጨማሪ በእጃችን ያሉትና ከዚህ ቀደም ያልተጠቀምንባቸው ቴክኖሎጂዎች ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ግንዛቤ አግቺያለሁ” ብለዋል።