ቀጥታ፡

በደን ልማት ለሚሳተፉ የግል ተቋማት መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል-የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ግንቦት 30/2010 ኢትዮጵያ ውስጥ በደን ልማት ለሚሳተፉ የግል ተቋማት መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ገለጸ። በዘርፉ የግል ተቋማት ተሳትፎ መጎልበት በሀገሪቷ በደን ምርት ውጤትና በኢንዱስትሪ መካከል ሊኖር በሚገባው ትስስር ዙሪያ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመቀነስ ያግዛል ሲልም ሚኒስቴሩ አመልክቷል። ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ከበደ ይማም ለኢዜአ እንደተናገሩት መንግስት የሀገሪቷን የደን ልማት ለማሳደግ የሚያስችልና የግሉን ዘርፍ ተሳታፊ የሚያደርግ የአስር ዓመት የደን ልማት መርሃ ግብር ቀርጾ ወደ ተግባር ገብቷል። ከዘርፉ ልማት ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ የነበሩ የመሬትና የብድር አቅርቦቶች አንደዚሁም የቴክኒክ ድጋፍ ችግሮች በልማት መርሃ ግብሩ አማካኝነት እንደሚፈቱም አቶ ከበደ ተናግረዋል። በልማቱ መሰማራት ለሚፈልጉ የግሉ ዘርፍ አካላት መንግስት ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋል ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው፤ ከዚሁ ጋርም ከሊዝ ነጻ መሬት፣ የገንዘብ ብድርና ሙያዊ ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችል  አዋጅ ተደንግጎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ነው ያሉት። በዘርፉ የሚሰማሩ የግሉ ዘርፍ አካላት አንድ የምርት ዘመን ከታክስ ነጻ ይደረግላቸዋልም ብለዋል። በመሆኑም በዘርፉ መሰማራት የሚፈልጉ የግል ተቋማት ተሳታፊ በመሆን በሀገሪቷ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመፍጠር በሚደረገው እንቅስቃሴ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ሚነስትር ዴኤታው አሳስበዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም