ቀጥታ፡

አራተኛው የደቡብ ክልል ፌስቲቫል እየተካሄደ ነው

ግንቦት 24/2011 አራተኛው የደቡብ ክልል የባህል ፌስቲቫል በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

“ባህላችን ለሰላማችንና ለአብሮነታችን” በሚል መሪ ቃል በሚከበረው 4ኛው ክልል አቀፍ ፌሲቲቫል ላይ ከሃገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የተወከሉ ልኡካንም እየተሳተፉ  ይገኛሉ፡፡

ፌሰቲቫሉን በምርቃት የከፈቱት የክልሉ የባህል ሽማግሌዎች የሃገርን ሰላምና ልማት እንዲሁም የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ውጤታማ ለማድረግ በጋራ መትጋት አለብን የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

አብረው ተዋግተው የአገርን ሉአላዊነት ማስከበራቸውን የተናገሩት የባህል ሽማግሌዎቹ አሁን በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ አለመግባባቶችን ለመፍታት ባህላዊ እሴቶች የጎላ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።

በመድረኩ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክትር ሒሩት ካሳው እና የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወክለው የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ክፍሌ ገብረማርያም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ፌቲቫሉ ለሦስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በዛሬው ዕለትም የብሔር ብሔረሰቦች ባህልና ወግን የሚያሳዩ ትርኢቶች፣ የምግብ አሰራር ዜዴዎችና ጭፈራዎች ለፌስቲቫሉ ተታዳሞዎች በመተዋወቅ ላይ ናቸው፡፡

በተጨማሪም የባህል ፌስቲቫል አውደርዕይ ተመርቆ ለተመልካች ክፍት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የተለያዩ ባህላዊ እሴቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት ዛሬ ከሰዓት በኋላ እንደሚደረግ ታውቋል ሲል የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም