ቀጥታ፡

የሴቶች እጅ ኳስ ሻምፒዮና ነገ ይጀመራል

ግንቦት 24/2011 የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች እጅ ኳስ ሻምፒዮና ነገ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ይጀመራል።

በሻምፒዮናው ላይ ከደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፣ከሐረሪና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አጠቃላይ 70 ተወዳዳሪዎች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሞላ ተፈራ ለኢዜአ እንደገለጹት የሻምፒዮናው አላማ ለዓመታት ተቋርጦ የነበረውን የኢትዮጵያ ሴቶች እጅ ኳስ ሻምፒዮና ዳግም እንዲጀመር ማድረግ ነው።

በሻምፒዮናው አስፈላጊውን ቅስቀሳ በማድረግ በቀጣዩ ዓመት የኢትዮጵያ ሴቶች እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ለማካሄድ ጥረት አንደሚደረግም ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በሁለቱም ጾታዎች የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ይካሄድ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሞላ ተወዳጅ የነበረው የእጅ ኳስ ስፖርት እየተቀዛቀዘ በመምጣቱና ስፖርቱን የማስፋፋት ስራው በሚጠበቀው ደረጃ አለመሰራቱ አገር አቀፍ ሻምፒዮናዎች እንዳይካሄዱ ማድረጉን አመልክተዋል።

የእጅ ኳስ ፌዴሬሽኑ በተያዘው በጀት ዓመት ካቀዳቸው እቅዶች መካከል የሴቶች እጅ ኳስ እንቅስቃሴ ዳግም ለማነቃቃት የኢትዮጵያ የሴቶች እጅ ኳስ ሻምፒዮናን ማዘጋጀት እንደሆነና ይሄን ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።

የኢዜአ ሪፖርተር የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና ሌሎች ቀሪ ስድስት ክልሎች በሻምፒዮናው ላይ ለምን አልተሳተፉም? በቂ የቅስቀሳ ስራ አልተሰራም ወይ? በሚል ለጽህፈት ቤት ሃላፊው ጥያቄ አቅርቧል።

ከሁለት ወር በፊት ፌዴሬሽኑ ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ክልሎቹና ከተማ አስተዳደሮቹ ሻምፒዮናው እንዲዘጋጅ የቀረበውን ሀሳብ አጽድቀው በሻምፒዮናው ላይ እንደሚሳተፉ ገልጸው እንደነበር አቶ ሞላ ገልጸዋል።

ፌዴሬሽኑ ለሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በደብዳቤ እንዳሳወቀና ድሬዳዋና የተቀሩት ስድስት ክልሎች በፋይናንስና ሌሎች ችግሮች ምክንያት እንደማይሳተፉ ማሳወቃቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ ሴቶች እጅ ኳስ ሻምፒዮና በየዓመቱ በዘላቂነት እንዲካሄድ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በቅንጅት እንደሚሰራም ነው አቶ ሞላ ያስረዱት።

በተያዘው ዓመት በክልሎችና በከተማ አስተዳሮች የሴቶች ስፖርት እንዲነቃቃ የሚያስችሉ የቅስቀሳ ስራዎች መካሄዳቸውንም አስታውሰው ቅስቀሳውም አበረታች የሚባል ውጤት እንዳስገኘም አክለዋል'

የ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች እጅ ኳስ ሻምፒዮና እስከ ግንቦት 30 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።

የእጅ ኳስ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በ1960 ዓ.ም በዩንቨርሰቲ ምሁራን ሲሆን ከጥቂት ዓመታት በኋላም ከፖሊስ፣ ከጦር ሃይሎችና ከልዩ ልዩ ክፍሎች የተወጣጡ ተሳታፊዎች ስለ ጨዋታው ስልጠና ተሰጥቷቸው ስፖርቱ እንዲዘወተር ምክንያት እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ስፖርቱን የመምራትና የማስፋፋት ሃላፊነት ተሰጥቶት በ1962 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን በ1986 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ሻምፒዮና ማካሄድ ጀመረ።

በሴቶች እጅ ኳስ ከ1968 እስከ 1975 ዓ.ም ከ10 ያላነሱ ክለቦች በኢትዮጵያ የሴት ክለቦች ሻምፒዮና ላይ ይሳተፉ እንደበርም መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በ1975 ዓ.ም የኢትዮጵያ የስፖርት አደረጃጀት በአዲስ መልክ በተዋቀረ ወቅት አንድ ስፖርተኛ በእንድ ስፖርት ብቻ ነው መሳተፍ የሚችለው በመባሉ የሴት እጅ ኳስ ክለቦች ሙሉ ለሙሉ ተበተኑ።

ከዛም በኋላ ስፖርቱ በወቅቱ የነበረው ዝና ጠፍቶ ስፖርቱ እየተቀዛቀዘ በምጣቱ ተዘውታሪነቱ እየቀነሰ መጣ።

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በወንዶች የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ እያካሄደ ሲሆን በሴቶች እጅ ኳስም የተለያዩ ቅስቀሳዎችን በማድረግ ስፖርቱ ዳግም እንዲያንሰራራ ጥረት እያደረገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም