በአንድ ኩይሳ ሁለት ሚሊዮን ምስጦች - ኢዜአ አማርኛ
በአንድ ኩይሳ ሁለት ሚሊዮን ምስጦች
ገብረህይወት ካህሳይ ከኢዜአ
ከሞጆ ወደ ሀዋሳ ሲጓዙ በዱግዳና ቦራ ወረዳዎች እሰከ መቂ ከተማ ድረስ ግራና ቀኙን ይመልከቱ ። በተለያዩ ቅርፆች የቆሙ ሃውልት መሳይ ነገሮች በብዛት ይታያሉ ። ታዲያ ! የጢያ ትክል ድንጋዮች አሊያም ሆነ ተብሎ ከአለት ተፈልፍለው የተሰሩ ሰው ሰራሽ ሃውልቶች አይደሉም - ኩይሳዎች እንጂ ።
በተለይ በዱግዳ ወረዳ ከሚገኙ 35 ቀበሌዎች መካከል በ32ቱ ቀበሌዎች ይዞታ በሺዎች የሚቆጠሩ ኩይሳዎች የእርሻ ማሳውን ወረውታል ። አንድ ኩይሳ በውስጡ ከሁለት እስከ ሶስት ሚሊዮን የሚጠጉ ምስጦች እንደሚይዝ የወረዳው አስተዳደር የግብርና ባለሙያዎች ይገልፃሉ ።
አቶ ባቲ አቡ በዱግዳ ወረዳ አስተዳደር የህዝብ ቅሬታ ሰሚ የስራ ሒደት ባለቤት ናቸው ። የወረዳው አርሶ አደሮች በኩይሳው ምክንያት መማረራቸውንና ተደጋጋሚ ቅሬታ አቅርበው መፍትሔ ማጣታቸውን ይናገራሉ ።
ኩይሳዎቹ ሜዳማውን የእርሻ ማሳዎች በማጣበብ ፣ ለእርሻ መካናይዜሽን ስራዎች አንቅፋት በመሆን ፣ በሰው ሃይል የታጨደው ነዶና ክምር በምስጦች እንዲጠፋና የመኖሪያ ቤቶችን በምስጦች ተበልተው እንዲወድቁ በማድረግ የአርሶ አደሩን አኗኗር እያወኩት ነው ይላሉ ።
እንዲያው ! በአንድ ወቅት በስካር መንፈስ ኩይሳ አጠገብ ወድቆ የተኛ አንድ ግለሰብ ጋቢውን በምስጥ ተበልቶ አልቆ ማደሩን አቶ ባቲ በማሳያነት ገልፀዋል ።
ኩይሳዎቹ ወደ ላይ ብቻ ሳይሆን ወደ ውስጥም እስከ ሶስት ሜትር የሚደርስ ጥልቀትና ስፋት አላቸው ። በአርሶ አደሩ አቅም ቆፍሮ መንቀል የማይታሰብ አስቸጋሪ ስራ ነው ይላሉ ።
በዱግዳ ወረዳ ግብርና ልማት ፅህፈት ቤት የሰብል ጥበቃ ባለሙያ አቶ አማን ገላሴ እንደሚሉት ኩይሳዎቹ በውስጣቸው ለቁጥር የሚታክት የምስጥ ብዛት አቅፈው የያዙ ናቸው ። የግብርናውን ስራ የሚፈታተኑት ደግሞ ገና ከዘር ወቅት ጀምሮ ነው ።
”በእርሻ ማሳ ላይ የተበተነውን ዘር እየለቀሙ በመብላት እንዲሳሳ ያደርጉታል ። የቡቃያውን ስር በመብላትም እድገቱ ያዳክሙታል ። የሰብል ክምር ከሁለት ቀናት በላይ በማሳ ማሳደር አይቻልም ። እየፈለፈሉ በመብላት ያጠፉታል ” ባይ ናቸው ።
በአንድ በኩል የህዝብ ቁጥር እየጨመረ በሌላ በኩል ደግሞ የእርሻ መሬት እየጠበበ በመጣበት ወቅት ኩይሳዎች መሬቶችን በመውረር ችግሩ ” በእንቅር ላይ ጆሮ ደገፍ ” አድርገውታል ይላሉ ።
በአሁኑ ወቅት በአንድ ቀርጥ በአማካይ ሰባትና ከዚያ በላይ ኩይሳዎች ቆመው ይታያሉ ። ይህ ቁጥር በአንድ ሔክታር በአማካይ ከ28 እስከ 30 ኩይሳዎች ይደርሳል የሚል ግምት አላቸው ። ቁጥሩ ወደ ምስጥ ብዛት ሲቀየር ደግሞ ወደ 60 ሚሊዮን ሊጠጋ ይችላል ።
ሎዶር ፣ ዶዘርና ግሬደር በመሳሰሉት ከባድ የግንባታ መሳሪያዎች በመታገዝ ካልሆነ በስተቀር ኩይሳን በእጅ ነቅሎ ማስወገድ እንደማይቻል ባለሙያው ገልፀው የክልልና የፌዴራል መንግስታት ለጉዳዩ ትኩረት ቢሰጡበት መልካም ነው በማለት አስተያየት ሰጥተዋል ።
አርሶ አደር ዶኒ አቡ በዱግዳ ወረዳ የኦዶ ቦቆ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ ኩይሳ ለዓመታት መፍትሄ ያላገኘ የአርሶ አደሩ ችግር ነው ይላሉ ። በኩይሳው ውስጥ የሚኖሩ ምስጦች የሰብል ምርትን ከማጥፋታቸው በላይ የእንጨት ቤቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከስር በልተው በመጣል ኑሮአችንን እያመሰቃቀሉት ይገኛሉ በማለት ብሶታቸውን ይገልፃሉ ።
አቅም ያለው የብሎኬት ቤት በመገንባት እፎይታ ሲጎናፀፍ አቅመ ደካማው ግን የእንጨት ቤት ሲገነባ መልሶ በምስጦች ሲወድቅበት ከኩይሳ ጋር ትንቅንቅ ገጥሞ ኑሮውን ለመግፋት ተገዷል በማለት የችግሩ አሳሳቢነት ያስረዳሉ ።
ችግሩ ካለመንግስት ድጋፍ የሚፈታ አይደለም የሚሉት አርሶ አደሩ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ብቻውን ምርታማነትን አያሳድግምና የእርሻ ማሳችንን እየነጠቀን ያለው ኩይሳ በማፈራረስ እገዛ ሊደረግልን ይገባል የሚል ሃሳብ አላቸው ።
አርሶ አደር ገና ዋሪ በበኩላቸው ህዝብ እየበዛ የእርሻ ማሳ ደግሞ እያጠረ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት ኩይሳዎች መሬትን እየተሻሙ የበለጠ እያጠበቡት መጥቷል ።
ካለችን መሬት ቆርሰን ለደረሱ ልጆቻችን ማካፈል ይቅርና በኩይሳ ምክንያት ለቤተሰብ የሚበቃ ዓመታዊ ቀለብ ማምረት ጭምር እየተሳነን ነው ሲሉ ብሶታቸውን ይገልፃሉ ። እሳቸውም እንደሌሎቹ አርሶ አደሮች የመንግስትን እገዛ ጠይቀዋል ።
በተለያዩ ጊዜያት አርሶ አደሩ በህብረት ኩይሳዎቹን ነቅሎ ለመጣል ሙከራዎች አድርጓል ። አንዱን ኩይሳ ከስር መሰረቱ ለማጥፋት ከሁለት ሳምንት በላይ እንደሚወስድም አርሶ አደሩ ይናገራሉ ። በዚህ ስሌት በአካባቢው እንደ አሸን የፈሉት ኩይሳዎች ለማስወገድ ሌላውን ስራ በመተው ጭምር ዓመታትን የሚጠይቅ ነው ይላሉ ።
ሌላው ችግር ከሚፈርሰው ኩይሳ የሚወጡት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምስጦች ወዲያውኑ በኬሚካል መግደልና ማጥፋት ካልተቻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሌሎች አዳዲስ ኩይሳዎች የመፍጠር ሃይል አላቸው ።
ለዚህም ነው መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ዘላቂ መፍትሔ ካላበጀለት የአርሶ አደሩ ጥረት ብቻውን የሚፈይደው ውጤት አይኖርም የምንለው ሲሉ ጥረታቸው ከንቱ መቅረቱን ያስረዱት ።
የወረዳው የህዝብ ቅሬታ ሰሚ የስራ ሒደት ባለቤት አቶ ባቲ አቡ የአርሶ አደሮች ቅሬታ በተደጋጋሚ ጊዜ በየደረጃው ለሚገኙ የመስተዳድር አካላት ቀርቦ በነገ ዛሬ መፍትሔ ሳያገኝ መቆየቱን ይናገራሉ ።
የትኩረት ማነስ እንጂ ኩይሳዎች በማሽነሪ ነቅሎ ማስወገድ ከሌሎች ችግሮች የገዘፈ አስቸጋሪ ስራ አይደለም ብለዋል ።
አሁን ግን በክልልና በፌዴራል ደረጃ ሃላፊነቱን የተረከበው የለውጥ ሃይል ችግሮችን ደረጃ በደረጃ እየፈታ በመሆኑ የኩይሳ ችግርም መፍትሔ ያገኛል የሚል እምነት አለኝ ብለዋል ።
የአቶ ባቲ እምነት ሰምሮ የህብረተሰቡ የዘመናት ጥያቄ መልስ ያገኝ ዘንድ መልካም ምኞታችንን እየገለፅን ችግሩ ከዚህ የበለጠ እንዳይስፋፋ ሁሉም ተገቢውን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል እንላለን ።