ቀጥታ፡

ድርጅቱ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማጠናከር እንደሚሰራ ገለፀ

አዲስ አበባ  ግንቦት 30/2010 የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማሳደግ ከትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር ለመስራት ማቀዱን የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት አስታወቀ። ድርጅቱ ከ'ፋም አቢሲኒያ የትራንስፖርትና ቱሪዝም ፐብሊኬሽን' ጋር በመተባበር የአገር ውስጥ የቱሪዝም ሃብትን በማስተዋወቅ ረገድ የመገናኛ ብዙሃን ሚናን የተመለከተ አውደ ጥናት አካሄዷል። በአውደ ጥናቱ ላይ ሶስት የመነሻ ፅሁፎች የቀረቡ ሲሆን፤ ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑንና በዚህም የተነሳ ትክክለኛውን የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር ለማወቅ እንዳልተቻለ ተጠቁሟል። በመሆኑም  የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን በመከታተል በቆጠራ የሚገኝ አሃዝ ሊኖር እንደሚገባም ነው በቀረቡት ጽሑፎች ላይ የተገለፀው። ከዚህ በተጨማሪም የመገናኛ ብዙሃን ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም ሃብትን በማሳወቅ ረገድ የሚያቀርቧቸው ዘገባቸው አነስተኛ በመሆናቸው ዘርፉን ለማሳደግ ሲባል የተጠናከሩ ስራዎች ሊከናወኑ እንደሚገባም ነው የተብራራው። የድርጅቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር የቻለ ምህረት በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በዛሬው እለት የተዘጋጀው የውይይት መድረክ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ማልማት በሚቻልበት መስክ ላይ ለመምከር ነው። በአሁኑ ወቅት በትምህርት ቤቶችና በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ያሉ 'የሀገርህን እወቅ ክበባት' የተቀዛቀዙ ሲሆን፤ በአዲሱ በጀት ዓመት እነዚህን ለማጠናከር መታቀዱን ነው ያመለከቱት። ''ሀገርን ማወቅ ማንነትን አውቆ ለሀገር ማበርከት የሚጠበቅብንን ለማበርከት የሚረዳ በመሆኑ ሁሉም ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም መጠናከር እገዛ ማድረግ አለበት'' ነው ያሉት። የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው በተጨማሪ ለሀገራዊ መግባባትና አንድነት ለመፍጠር የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለውም ነው የተናገሩት። በመሆኑም  የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በትብብር በመስራት ተማሪዎች ሀገራቸውን እንዲጎበኙ ለማድረግ እንደሚሰራም ገልፀዋል። የሀገር ውስጥ ጎብኚውን ቁጥር ለማሳደግና ያሉ ችግሮችን ለማስወገድ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ማስፋፊያ ስትራቴጂ ዝግጅት በወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅም ተናግረዋል። የ'ፋም አቢሲኒያ የትራንስፖርትና ቱሪዝም ፐብሊኬሽን' ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፍሬው አበበ በበኩላቸው ድርጅቱ በሀገሪቱ የቱሪዝም ልማትና እድገት የራሱን አስተዋፅኦ ለማበርከት በአውደ ጥናቱ ዝግጅት መሳተፉን ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም