ቀጥታ፡

በነገው የሊጉ ጨዋታ መከላከያ ሲዳማ ቡናን ያስተናግዳል

አዲስ አበባ ግንቦት 23/2011የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ

ነገ  ከቀኑ 10 ሠዓት የመውረድ ስጋት ውስጥ የሚገኘው መከላከያ በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲዳማ ቡናን ያስተናግዳል።

በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲ ከአዳማ ከተማ፣ በሀዋሳ ስታዲየም በደቡብ ደርቢ ደቡብ ፖሊስ ከሀዋሳ ከተማ በተመሳሳይ ከቀኑ በዘጠኝ ሠዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ከነገ በስቲያ ከቀኑ 10 ሠዓት ኢትዮጵያ ቡና መቐለ ሰብዓ እንደርታን  በአዲስ አበባ ስታዲየም ያስተናግዳል።

በክልል ከተሞችም አራት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

በአፄ ፋሲለደስ ስታዲየም የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ፋሲል ከነማ ከባህርዳር ከተማ፣ በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከፕሪሚየር ሊጉ መውረዱን ያረጋገጠው ደደቢት ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ በሶዶ ስታዲየም ወላይታ ድቻ ከጅማ አባ ጅፋር እና በድሬዳዋ ስታዲየም ድሬዳዋ ከተማ ከስሑል ሽረ በተመሳሳይ ከቀኑ በዘጠኝ ሠዓት ይጫወታሉ።

አራት ጨዋታዎች በቀሩት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ለማንሳትና ላለመውረድ የሚደረገው ፍልሚያ አጓጊ እየሆነ ሲሆን የእያንዳንዱ ሳምንት መርሃ ግብሮች ዋንጫ የሚያነሳውንና ከፕሪሚየር ሊጉ የሚወርዱትን ክለቦች የሚለዩ ናቸው።

የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ፋሲል ከነማ፣ መቐለ ሰብዓ እንደርታና ሲዳማ ቡና በተመሳሳይ 49 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

መከላከያ፣ ደቡብ ፖሊስና ከፕሪሚየር ሊጉ መውረዱን ያረጋገጠው ደደቢት ከ14ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

በፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫውን ለማንሳትና ላለመውረድ እንደሚደረገው ፉክክር ሁሉ የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢነት የሚካሄደው ፉክክርም አጓጊ ሆኗል።

የፕሪሚየር ሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የመቐለ ሰብዓ እንደርታው አማኑኤል ገብረሚካኤልና የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ በተመሳሳይ 15 ግቦች ሲመሩ፣ የደቡብ ፖሊሱ ሄኖክ አየለና የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም በተመሳሳይ 12 ግቦች ይከተላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም