ቀጥታ፡

የኤሌክትሪክ ኃይል የማይደርስባቸውን አካባቢዎች ተጠቃሚ ማድረግ የሚያሰችል ስምምነት ተደረገ

አዲስ አበባ ግንቦት 23/2011 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል የማይደርስባቸውን አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ ከሦስት የቻይና ኩባንያዎችና ከአንድ የስፔን ኩባንያ ጋር የውል ስምምነት አደረገ። 

ኖራንኮ ኢንተርናሽናል፣ ጉድያን ናንጂንግ፣ ሲኢቲና ኤን አር የተባሉ የቻይና ኩባንያዎች እንዲሁም ትራማ የተባለ የስፔን ኩባንያ የውል ስምምነቱን ፈርመዋል።  

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሽፈራው ተሊላ እንደገለጹት፤ በአገሪቱ የሚገኙ ከተሞችንና የገጠር መንደሮችን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ የኤሌትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ ያስፈልጋል።

ተቋሙ ፍትሃዊ የኤሌትሪክ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ከብሔራዊ የኃይል ቋት ውጭ ኤሌትሪክ በማመንጨት ለህብረተሰቡ ለማዳረስ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።  

ከብሔራዊ የኃይል ቋት ውጭ የሆኑ 12 አነስተኛ የሙከራ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ግንባታ ለማከናወን በዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ የአገሪቱን ክልሎች በስድስት መደብ በመክፈል 12 የገጠር ከተሞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን በምድብ አንድ በኦሮሚያ፣ በምድብ ሁለት በአማራ፣ በምድብ ሦስት በደቡብ፣ በምድብ አራት በሶማሌና ኦሮሚያ፣ በምድብ አምስት በአፋርና ትግራይ እንዲሁም በምድብ ስድስት በጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እንደሚከናወን አቶ ሽፈራው አመልክተዋል።

ከዓለም ባንክ በተገኘ 8 ሚሊዮን 516 ሺህ 758 ዶላር እና የኢትዮጵያ መንግስት በመደበው 59 ሚሊዮን 614 ሺህ 998 ብር የሚከናወን ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ በ6 ወራት ውስጥ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የሚጀምር ሲሆን ከ67 ሺህ በላይ የገጠር አካባቢ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።   

ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ሲደረግም የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚገኝበት፣ አዳዲስ የስራ ዕድል የሚፈጠርበት እና የኃይል አማራጮችን የሚያሰፋ እንደሆነ የገለጹት ዋና ስራ አስኪያጁ ''67 ሺህ 753 አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌትሪክ ተጠቃሚ ያደርጋል'' ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በተደረገው ኤሌክትሪክ የማዳረስ ስራ 7 ሺህ 47 ከተሞችና የገጠር መንደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።   

በተያዘው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ 130 አዳዲስ የገጠር መንደሮችንና ከተሞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ተናግረዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም