''በአመራር አባላቶቹ መካከል ያለውን አለመግባባት ከኢዜማ ጋር አያይዘን አናየውም''-ብርቱካን ሚደቅሳ - ኢዜአ አማርኛ
''በአመራር አባላቶቹ መካከል ያለውን አለመግባባት ከኢዜማ ጋር አያይዘን አናየውም''-ብርቱካን ሚደቅሳ
አዲስ አበባ ግንቦት 23/2011በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢዴፓ) አመራሮች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች የተመሠረተው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ ጋር እንደማይገናኝ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ኢዴፓ በፓርቲነት ተመዝግቦ ለረጅም ጊዜ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
ይሁንና ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በፓርቲው አመራሮች መካከል የነበረውን ክርክርና አለመግባባት ቦርዱ ውሳኔ እየሰጠ ቢቆይም ፓርቲውም ውሳኔው በአግባቡ እየተፈጸመ አለመሆኑን በቅሬታ ሲገልጽ መቆየቱን ገልጸዋል።
ይሁንና በቅርቡ ኢዴፓን ጨምሮ ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች አዲስ ፓርቲ ለመመስረት ለቦርዱ የፓርቲ ምዝገባ ጥያቄ አቅርበዋል።
''በአመራር አባላቶቹ መካከል ያለውን አለመግባባት ከኢዜማ ጋር አያይዘን አናየውም'' ያሉት ሰብሳቢዋ ኢዜማ ለቦርዱ ያቀረበው ጥያቄ እንደ አዲስ በፓርቲነት የመመዝገብ እንጂ የውህደት ጥያቄ አለመሆኑን ገልጸዋል።
ውህደትና በአዲስ ፓርቲነት የመመዝገብ ጥያቄዎች የተለያዩ መሆናቸውን የገለጹት ወይዘሪት ብርቱካን ፓርቲው እንደ አዲስ የመመዝገብ ጥያቄ ያቀረበ በመሆኑ ቦርዱ በአዲስ ፓርቲነት ለመመዝገብ የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን መሟላት አለመሟላቱን እያጣራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በዚህ መሰረት በህግና ደንቡ መሰረት የፓርቲ አባላቱ ስም ዝርዝርና ፊርማ ጠቅላላ ጉባኤ መደረግ አለመደረግና ሌሎች ጉዳዮችን እየተፈተሸ መሆኑን ነው የገለጹት።
በቅርቡ ኢዴፓ ጠቅላላ ጉባኤ ማድረጉን ጠቅሰው ''ጠቅላላ ጉባኤው በህጉ መሰረት የተደረገ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ቦርዱ እየመረመረ ነው'' ብለዋል።
በሌላ በኩል ጠቅላላ ጉባኤው የተጠራው ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ነው የሚሉ ወገኖችም ቅሬታ እየታየ እንደሆነ ገልጸዋል።
በዶክተር ጫኔ ከበደ የሚመራው አመራር መጨረሻ ላይ ያደረገው ምርጫ ያልተለወጠ ቢሆንም ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ ከነበረበት ጊዜ ሁለት ዓመት ከአምስት ወር እንዳለፈውም ነው ወይዘሪት ብርቱካን ያስታወቁት።
እነዚህንና ሌሎች ጉዳዮችን ጨምሮ የፓርቲውን አመራሮች ክርክሮች ቦርዱ በአግባቡ እየመረመረ ሲሆን በቅርቡ ህጋዊ ውሳኔ እንደሚሰጥ አመላክተዋል።
በሌላ በኩል ከዚህ በፊት የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ወደ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና ብሄረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ወደ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ስማቸውን ሲቀይሩ ለቦርዱ ሳያሳውቁ መቆየታቸውን አስታውሰው በቅርቡ ፓርቲዎቹ የጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ሰነዶቻቸውን አሟልተው ማቅረባቸውን ገልጸዋል።