የሲዳማ ብሔር ፍቼ ጫምበላላ በዓል በሰላም ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
የሲዳማ ብሔር ፍቼ ጫምበላላ በዓል በሰላም ተጠናቀቀ
ግንቦት 23/2011 በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የሲዳማ ብሔር ፍቼ ጫምበላላ በዓል በሰላም መጠናቀቁን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ጸጥታውን በማስተባበር ረገድ የአካባቢው ወጣቶችና የከተማው ነዋሪዎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ተገልጿል፡፡
የሃዋሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር መስፍን ዴቢሳ እንደገለጹት በዓሉ ከመከበሩ አስቀድሞ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ከከተማው ነዋሪ ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡
የከተማና ዞን ፖሊስ፣ የክልሉ ልዩ ኃይል፣ የፌደራል ፖሊስና መከላከያ ሠራዊት በመቀናጀት በበቂ ዝግጅት ወደስራ መግባታቸውን አስታውሰው ይህም “በዓሉ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ አድርጓል” ብለዋል፡፡
ፖሊስ አዛዡ እንዳሉት የጸጥታ ስራውን በማገዝ ረገድ ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሲዳማ ወጣቶችና የከተማው ነዋሪ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡
በቅንጅት በተሰራው ስራም 24 የሚሆኑ በስርቆት ወንጀል የተሳተፉና ሁከት ለመፍጠር የሞከሩ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡
ከነዚህ ውስጥም 10ሩ ለበዓሉ በተቋቋመው ተዘዋዋሪ ችሎት አማካይነት ውሳኔ ያገኙ ሲሆን ቀሪዎቹ ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር የህዝብ ግንኙነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መልካሙ ተፈራ በበኩላቸው በዓሉ የአለም ቅርስ መሆኑን ተከትሎ በርካታ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት ተደርጎ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
“ታዳሚው ራሱን የበዓሉ ባለቤት አድርጎ አክብሯል” ያሉት ኃላፊው፣ በዓሉ በተከናወኑ የጎዳና ላይ ትርኢቶችን ጨምሮ በበርካታ ዝግጅቶች የታጀበ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ከፀጥታ መዋቅሩ፣ ከህዝቡና ከወጣቱ ጋር በቅንጅት በተሰራው ሥራ በዓሉ በደመቀና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መጠናቀቁንም ገልጸዋል፡፡
የከተማው ህዝብም እንግዶችን በተገቢው መንገድ አስተናግዶ በመሸኘቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡