ቀጥታ፡

በስፖርቱ ዘርፍ የሚካሄዱ ጥናትና ምርምሮች ተግባራዊ እንዲሆኑ አሰራር ሊዘረጋ እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ ግንቦት 23/2011በስፖርቱ ዘርፍ የሚካሄዱ ጥናትና ምርምሮች ወደተግባር እንዲቀየሩ የሚያስችል የቅንጅት አሰራር ስርአት ሊዘረጋ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ገለጸ።

በአካዳሚው አዘጋጅነት ለሁለት ቀናት የሚካሄደው 6ኛው ዓመታዊ አገር አቀፍ የስፖርት ሳይንስ የጥናትና ምርምር ጉባኤ ዛሬ ተጀምሯል።

የአካዳሚው ዋና ዳይሬክተር አቶ አንበሳው እንየው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ አካዳሚው ከአምስት ዓመት በፊት ስራ ሲጀምር ከተሰጡት ተልዕኮዎች አንዱ በስፖርቱ ዘርፍ ችግር ፈቺ የሆኑ ጥናቶችና ምርምሮችን ማድረግ ነው።

ይህንን ተልዕኮ መሰረት በማድረግ አካዳሚው የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን እያካሄደ መሆኑንና ዓመታዊ የስፖርት ሳይንስ ጥናትና ምርምር ጉባኤዎችን እያካሄደ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

አካዳሚው ከሚያደርጋቸው ጥናትና ምርምሮች ውስጥ በስፖርተኞች ስልጠና ምልመላና በስፖርት አደረጃጀት ላይ ያሉበትን ክፍተቶችን ለመሙላት እየተጠቀመበት ቢሆንም ተግባራዊ ከመሆንና የስፖርቱን ችግሮች ከመፍታት አንጻር የሚጠበቀውን ማከናወን እንዳልተቻለ አመልክተዋል።

ጥናትና ምርምሮች ወደተግባር እንዳይገቡ እንቅፋት እየሆነ ያለው ጥናትና ምርምሮችን ተግባራዊ ማድረግ ያለባቸው ባለድርሻ አካላትንና ተመራማሪዎችን የሚያገናኝ የአሰራር ስርአት ባለመኖሩ እንደሆነ ጠቁመዋል። በመሆኑም ቅንጅታዊ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት እንዳለበት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በቀጣይም የስፖርት ባለሙያዎችን አቅም በማጎልበትና ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር ለህብረተሰቡ ማሰራጨት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀብታሙ ሲሳይ በበኩላቸው ስፖርት ያለ ሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር ውጤታማ መሆን ስለማይችል በዘርፉ የሚካሄዱ ጥናትና ምርምሮችን ለማካሄድና ወደተግባር ለማስገባት ባለድርሻ አካላት ተቀራርበው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ችግር ፈቺ የስፖርት ጥናትና ምርምሮችን ተደራሽ ለማድረግ ጠንክሮ እንዲሰራ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉና ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ ጥናትና ምርምሮች እንዲደረጉ፣ የተመራማሪዎችን አቅም በማጎልበትና ጥራት  እንዲኖራቸው የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር ዶክተር በዛብህ ወልዴ ''በስፖርቱ ዘርፍ የሚደረጉ ጥናትና ምርምሮች መደርደሪያ ላይ ከመቀመጥ ያለፈ ውጤት እያመጡ አይደለም'' የሚለው ሂስ ተገቢ እንደሆነ ያነሳሉ።

ለዚህም እንደ ችግር የሚነሳው ጥናቶች ሲደረጉ ነባራዊ ሁኔታን ያላገናዘቡ ጥናትና ምርምሩ ተደራሽ የሚያደርጋቸውን አካላት በጥናት ውስጥ ላይ በሚፈለገው ደረጃ አለማሳተፍ፣ የጥናትና ምርምር በጀት ማነስ እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

መንግስት ለስፖርት ጥናትና ምርምር የሚያደርገውን ትኩረትና የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ እንዳለበትና ባለድርሻ አካላት ተነጋግረው በጋራ መስራት የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው ስድስተኛው አገር አቀፍ ዓመታዊ የስፖርት የጥናትና ምርምር ጉባኤ 23 የጥናትና ምርምር ውጤቶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው የወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል።

አካዳሚው ባለፉት አምስት የስፖርት ሳይንስ ጥናትና ምርምር ጉባኤዎች ላይ ላይ በራሱ ወጪና በባለሙያዎች ፍላጎት የሚሰሩ የስፖርት የምርምር ስራዎችን በየዓመቱ እንዲቀርቡ እያደረገ ሲሆን በአምስቱ ጉባኤዎች 120 የሚጠጉ የምርምር ስራዎች እንዲቀርቡ አስችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም