ቀጥታ፡

የምርምር ቴከኖሎጂዎችን በማፍለቅ ለማህበራዊና ኢኮኖሚዊ እድገት ያላቸውን ሚና እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ

ግንቦት 23/2011 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል  ከማፈራት  ጎን ለጎን የምርምር ቴከኖሎጂዎችን በማፍለቅ  ለማህበራዊና  ኢኮኖሚዊ እድገት  ሚናቸውን እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ።

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ሦስተኛው ሀገር አቀፍ የምርምር ጉባኤ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ  ተጀምሯል።

የጋምቤላ ምክር ቤት አፍ- ጉባኤና የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ  አቶ ላክደር ላክባክ ጉባኤውን በንግግር ሲከፈቱ እንዳሉት ዩኒቨርሰቲዎች ከሰባዊ ልማት  ባለፈ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅና ልማትን በማፋጠን ረገድ አስተዋጿቸውን ሊያጠናከሩ ይገባል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሀገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚያፈልቋቸው የምርምር  ውጤቶችና እንደ ሀገር በቴክኖሎጂው ዘርፍ በሚከናወኑ ምርምሮች ከፍተኛ ማህበራዊ ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑንም አቶ ላክደር ተናግረዋል።

በመሆኑም የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ እንደ ሌሎቹ የትምህርት ተቋማት የምርምር  ቴከኖሎጂዎችን በማፍለቅ ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ  ተጠቃሚነት  የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡጁሉ ኡኮክ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት  “ዩኒቨርሰቲው እያከናወነ ካለው የሰው ሀብት ልማት ጎን ለጎን የምርምር ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅ ለማህበረሰቡ ሁለንተናዊ ለውጥና ተጠቃሚነት እየሰራ ነው” ብለዋል።

እንደ ዶክተር ኡጁሉ ገለጻ በምርምር ጉባኤው ከሚቀረቡት ጥናታዊ የምርምር ጸሁፎች  ለአካባቢው ማህበረሰብ የሚሆኑ ልምዶችንና ቴክኖሎጂዎች መለዋወጥም የጉባኤው  ሌላው አላማ ነው።

ሳይንሳዊ ምርምሮች በኢትዮጵያ ልማትን ለማስፋፋትና የፈጠራ ሥራዎችን ለማስፋፋት ለተነደፈው ሀገራዊ ፖሊሲ ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው  የምርምርና ማሀበረሰብ አቀፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ጋልዋክ ጋርኮስ ናቸው።

በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው የተቀየሱት ፖሊስዎችና የልማት እቅዶች እውን እንዲሆኑ የተጠናከረ የምርምር ሥራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም