ቀጥታ፡

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የቀድሞ ኃላፊዎች ላይ ያሉትን ምስክሮች ሊያሰማ ነው

አዲስ አበባ ግንቦት 23/2011 የፌዴራሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ የቀድሞ ኃላፊዎች ላይ ያሉትን ምስክሮች ሊያሰማ ነው።

በእነ አቶኃይለስላሴ ቢሆን መዝገብ ክስ የቀረበባቸው አቶ ኃይለስላሴ ቢሆን፣ አቶ የማነብርሃን ታደሰ፣ አቶ ሙከሚል አብደላ፣ ኢንጂነር አሸናፊ ሁሴን (ያልተያዙ)፣ አቶ ያሬድ ይገዙ፣ አቶ አንዳርጋቸው ሞግሪያ (ያልተያዙ) እና አቶ ያለው ሞላ ናቸው፡፡

ተከሳሾቹ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ቀርበዋል።

ተከሳሾቹ የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘትና ጥቅሙን ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ፣ የተሰጣቸውን ሥልጣንና ኃላፊነት በመጠቀም የመንግሥት ግዥ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 649/2001 አንቀጽ 52 ድንጋጌንና የማስፈጸሚያ መመሪያው አንቀጽ 25 እንዲሁም የኤጀንሲውን የግዥ መመሪያ አንቀጽ 10/3 በመተላለፍ፣ የወንጀል ድርጊቱን እንደፈጸሙ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ግንቦት 13 ቀን 2011 ዓ.ም ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ ዐቃቤ ሕግ ባቀረበባቸው ክስ ላይ መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ ለግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም ቀጠሮ ይዞ የነበረ ቢሆንም ተከሳሾቹ በተመሰረተባቸው ክስ ላይ መቃወሚያ የሌላቸው መሆኑን በመግለጻቸው በስነስርአት ሕጉ 130 እና 131 መሰረት የእምነት ክሕደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተደርጓል። 

በሰጡት የእምነት ክሕደት ቃል በወቅቱ ወይም ስራ ላይ በነበሩበት ወቅት ሕግና ደንብን ተከትለው መስራታቸውንና ወንጀሉንም እንዳልፈፀሙ ለችሎቱ መናገራቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ ክደው የተከራከሩ በመሆኑ አለኝ የሚላቸው ምስክሮችና ማስረጃዎች ቀርበው እንዲሰሙለት ጠይቋል።

ፍርድ ቤቱ በዚሁ መዝገብ ተከሰው በቁጥጥር ስር ካልዋሉት ተከሳሾች ቀጠሮ ጋር ጉዳያቸው እንዲታይና ቀጠሮ እንዲሰጥም ለዛሬ ግንቦት 23 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር።

በዚህም መሰረት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሐምሌ 19 ቀን 2011 ዓ.ም ምስክሮቹን እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም