ቀጥታ፡

ብዙ ሆነን… አንድ የሚያደርገን

በሰውነት ጀምበሩ (ኢዜአ)

አገር በእናት የምትመሰልበት ምክንያት በጉያዋ እቅፍ ድግፍ አድርጋ የምትይዝ ሆደ ሰፊ በመሆኗ ብቻ ሳይሆን፤ ለሁሉም የቤተሰብ አባላት ሳታዳላ እና ሁሉን ማዕከል ባደረገ መልኩ እንደየጸባዩና ባህሪው ለራበው ምግብ፤ ለጠማው ደግሞ ውሃ በእናትነት ፍቅሯና ፈገግተዋ ስለምትለግስ ነው። አገርም እንደ ጥሩ እና ብዙ ቤተሰብ እንዳላት እናት ትመሰላለች። በተለይ ኢትዮጵያ የብዙ ብሄር ብሄረሰቦች እና ቋንቋዎች ባለቤት የሆኑ ህዝቦችን፤ በየዘመናቱ የፖለቲካ ማዕበል ቢያላጋትም እቅፍ ድግፍ አድርጋ ለዘመናት ቆይታለች። በዚህ በልዩነት ላይ የዳበረው አንድነት በአለም ላይ ካሉ ውስን አገራት ቀዳሚ ያደርጋታል።

ይህ ለዘመናት የቆየው የመቻቻልና የአንድነት መንፈስ እየተሸረሸ መጥቶ አሁን ላይ ደርሰናል። በዋናነት ለዚህ እኛን ለማይመስለው ደባል ጸባይና እኩይ ተግባር በህገ መንግስት ማዕቀፍ ውስጥ ገብቶ ልዩነታችንን ብቻ በሚያጎላ መልኩ መሰራቱ እንደሆነ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት በቅርቡ ያወጣው መግለጫ ያስረዳል። በመሆኑም ይህን ለዘመናት አብሮ የቆየውን የጋራ እሴትና የአንድነት መገለጫ በዚህ ጊዜ በአገራችን ሥር ከሰደደው የጋራ ጠላታችን ‹ጥላቻ እና ቂም› ተላቀን አገራችንን ወደ ክብር ማማ የምናወጣበት፣ የእያንዳንዳችንንና የጋራችን ክብር የምናስመልስበት ብቸኛ የዘላቂ ሠላማዊ መፍትሄ አማራጭ እንደሆነ በየጊዜው ምሁራን ያሳስባሉ።

ስለዚህ ስለሁላችንና የሁላችን አገር ኢትዮጵያ ጉዳይ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ተቀራርበን እንነጋገር፣ ብሄራዊ መግባባት እንፍጠር፣ ካለፉት የጭቆና ሥርዓቶች ጥፋትና ጉድለቶች ተምረን፤ ዕርቅ አውርደን፤ያለፈው በማይደገምበት ቃል ኪዳንና የጋራ መርህ እጅ ለእጅ ተያይዘን በአንድነት ለሁላችን የምትመች፣ አዲስቱን ኢትዮጵያ ለመገንባት ወደፊት እየተመለከትን እንሂድ ሲል ነው የብሄራዊ ዕርቅና ይቅርታ ኮሚሽን ያሳሰበው። ኮሚሽኑ አክሎም የዘረኝነት፣ ጠባብነት፣ ጥላቻ ፖለቲካና የተናጠል አሸናፊነት፣ ኢፍትሃዊ፣ አግላይ የሆነ አመለካከትን በብሄራዊ እርቅ ለመተካት በአንድነት እንረባረብ በማለትም ያሳስባል።

ይህ በህብረ ብሄር ያበበ ማንነታችን ውበታችንን የበለጠ በማጉላት አንድ መሆን እንዳለብን መረዳት የግድ ይሆናል። ነገር ግን ከሁለት አስርት አመታት በላይ ልዩነታችንን በሚያጎላ መልኩ መሰራቱ አገራዊ አንድነታችን የተሸረሸረ እንደሆነ ምሁራን ያስረዳሉ።

ህብረ ብሄራዊነት የውበት መለኪያ ብቻ ሳይሆን፤ የጥንካሬም  መለኪያ በመሆኑ የተለያየ ጥበብ፣ የተለያየ መረዳት ውስብስብ የሆነውን የሰው ልጆች ፍላጎት ለማርካት አማራጮችን ይሰጣል። በመሆኑም ኢትዮጵያ ከሰማንያ በላይ ብሄሮችና ነገዶች ያሏት ሃገር በመሆኗ የውበትና የጥንካሬ ማማ እንጂ እንደ ችግር ሊሆን ባልተገባ ነበር።

እናም የኢትዮጵያ ሕዝብ ዳር እስከ ዳር በጥብቅ የሚያቆራኙት የጋራ እሴቶች ባለቤት በመሆኑ እና እነዚህ እሴቶች በኢትዮጵያዊነት ጠንካራ ገመድ የተያያዙ የኅብረ ብሔራዊ አንድነቱ ጌጦች ናቸው፡፡ በአራቱም ማዕዘናት በተለያዩ መልከዓ ምድራዊ አሠፋፈሮች ውስጥ ሆነው በሥነ ልቦና ከፍተኛ የሆነ መቀራረብና መወራረስ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ ልዩነቶቻቸውን ጌጥ አድርገው በአንድነት ለዘመናት አብረው ኖረዋል፣ አሁንም እየኖሩ ነው፡፡ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ቋንቋና የመሳሰሉትን ልዩነቶች አቻችለው በመተሳሰብና በመፈቃቀር ብቻ ሳይሆን፣ ተጋብተውና ተዋልደው ደግና ክፉ ጊዜያትን አብረው ያሳለፉት ኢትዮጵያውያን በማስተዋል የተሞሉ ናቸው፡፡

ነገር ግን በአንድም በሌላም ምክንያት አገሪቱን ምጣድ፣ ህዝቡን ማገዶ ወቅታዊ ስሜታቸውና ፖለቲካቸውን ደግሞ ዕሳት አድረገው ዳቦ ለመጋገር ያሰቡ፤ ያለፈውን ቂም በቀል እርሾ፣ ጊዜያዊ ፍላጎታቸውን ዱቄት አድርገው እያቦኩ ያሉ በርካታ አካላት እንዳሉ መጋቢአዲስ እሸቱ አለማየሁ ጦቢያ መድረክ ላይ ተናግረዋል። የእምነት አባቱ አክለውም አገር እንደ አገር እነዚህ እኩይ ሰዎችና አጥፊ ተግባራቸው መጠቀሚያ ባለመሆን የቆየውን አብሮ የመኖር ዕሴቶችን መጠበቅ እንደሚገባም በአጽንዕኖት ተናግረዋል።

አንዱ የሌላውን እያከበረና እያስተናገደ ልዩነቶች መኖራቸው እስከማያስታውቅ ድረስ አብረው የኖሩት ኢትዮጵያውያን አገራቸውን በጋራ ሲጠብቁ ኖረዋል ሲሉም አስረድተዋል፡፡ አንድም ጊዜ ለወራሪዎች ሳይንበረከኩ በተባበረ ክንዳቸው አሳፍረው መልሰዋል ያሉት የዕምነት አባቱ፤ ለዚህም ማሳያው በተለያዩ ዘመናት የተነሱ ገዥዎች ከበጎ ተግባራቸው በተጨማሪ ያደረሱዋቸውን በደሎችም፣ የኢትዮጵያዊነት ታላቁን ምሥልና የጋራ እሴቶችን በማስቀደም በመከባበርና በመተባበር አብረው እንዳሳለፉ አብራርተዋል፡፡ ይህንን የመሰለ ማስተዋል፣ አርቆ አሳቢነትና የአገር ፍቅር የተሞሉበት የጋራ እሴቶችን የሚንዱ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ ከምልክትነት በላይም አስፈሪ እየሆኑ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ድርጊቶች መቆም አለባቸው ሲሉም ያስረዳሉ።

ይህም የጋራ ዕሴቶቻችን በርካታ ውስብስብ ችግሮች ባሉበት አገር ውስጥ ልዩነቶችን በሠለጠነ መንገድ እንድናስተናግድ ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ፉክክር ራስን ማዘጋጀት ሲቻል፣ በዘመናት ችግሮች ላይ ተጨማሪ ችግሮችን እየፈጠሩ አገርን ማተራመስ የኋላቀርነት ትልቁ ማሳያ ነው፡፡ ለዚህ ችግርም በዋናነት ህዝቡ ሳይሆን እየተከናወነ ባለው  አገራዊ ለውጥ አንድም በአቅም ማነስ በሌላ በኩል ደግሞ ለውጡን በማደናቀፍ አገራዊ አንድነት እንዳይዳብር በሚመስል መልኩ ለዘመናት አብሮ እየኖሩ ያሉ ህዝቦችን እንዲጣሉ እና መፈላቀል እንዲመጣ የየአካባቢው የመንግስት ሹመኞች ዋና ተዋናይ እንደሆኑ በቅርቡ በቤንሻንጉል ክልል ውስጥ ለፍርድ የቀረቡት የመንግስት ሀላፊዎች ማሳያ ነው።

ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ ለ28ኛው ግንቦት ሃያ ክብረ በዓል ባስተላለፉት መልዕክታቸው ላይ “አቁሳይ አገዛዝ  እንጂ አቁሳይ ህዝብ የለም” ሲሉ የተናገሩት። ይህም በሕዝብ መሀል መሠረታዊ ቅራኔ ሳይኖር እርስ በርሱ ማጋጨት፣ በሰላማዊ መንገድ ተነጋግሮ መፈታት ያለበትን ጊዜያዊ ችግር የማይታረቅ ቅራኔ በማድረግ ግጭት መቀስቀስ፣ ትናንት አምባገነንነትን እና ከፋፋይ ስርዓትን በሕይወት መስዋዕትነት ለውጥ የወለደውን ወጣት ትውልድ በማታለል ወይም በፕሮፓጋንዳ በመመረዝ ለጥፋት ማሰማራትና የአገርን ሰላም ማደፍረስ ከፀረ ሕዝብነት ውጪ ሌላ ስያሜ ሊኖረው እንደማይችል ማሳያ ነው።

በዚህ እኩይ ተግባር ምክንያት በኢትዮጵያዊያን ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የነበሩ የጋራ እሴቶች እየተናዱ፣ ማንነትን መሠረት ባደረጉ ከፋፋዮች የአንድ አገር ልጆች መሀል የጠላትነት ግንብ እየተገነባ ይገኛል። በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ከፍተኛ ተከታዮችን ያፈሩ ግለሰቦች የዘር፣ የቋንቋ፣ የእምነትና የባህል ልዩነቶችን ከመጠን በላይ እየለጠጡ ለዘመናት አንድ ላይ የኖረ ሕዝብን እየነጣጠሉ ነው፡፡ ከልዩነቶቹ ይልቅ አንድነቶቹ የሚበልጡበትን፣ ተመሳሳይ ሥነ ልቦና ስለሚጋራ ተጋብቶና ተዋልዶ ዘመናትን የተሻገረን ሕዝብ በግድ በመለያየት ሆድና ጀርባ እያደረጉ ያሉ እነዚህ ግለሰቦች፣ በጊዜ ሃይ ሊባሉ ባለመቻላቸው ሞትና ስደት መስማት የየቀኑ ዜና ሆኗል።  

ከታሪክ እንደምንረዳው ኢትዮጵያዊነት የሰከነ ስሜት፣ የነቃ ህሊና በመሆኑ  የግብረ ገብ ሥነ-ልቦና አንድነትና የአፋዊ ሥርዓት ህብር ነው።   የጋራ ባህላችን በአንድ ቃል ከተነገረ ግብረ ገባዊ የጋራ ባህል ነው። ልዩ ልዩ ብሔረሰቦች ስርአቶችና ስነ - ስርዓቶች ሊለያዩ ቢችሉም፣ በግብረ ገብ ስነ ልቦና አንድ ናቸው፡፡ ደራሲ አያልነህ ሙላት እንዳሉት፣ የኢትዮጵያ ህዝብና ማህበረሰቦች በአንድ መደብ የበቀሉ አበቦች ናቸው፡፡ በዚህም ብዝሀነታችንን የሚያስተሳስረን አገራዊ ስሜታችንና እትብታችን ጉልህ ነው በማለትም ያስረዳሉ።

በተመሳሳይ የታሪክ ምሁሩ ዶ/ር ኃይሌ ወልደሚካኤል ‹‹አብሮነት በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ አነስ ያለ ታሪካዊ ጥናት በ1994 ዓ.ም. በወጣ መጽሐፋቸው ላይ እንደ ገለጹት ለጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የሚያስፈልገው ከዘረኝነትና ከራስ ወዳድነት መፅዳት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአጠቃላይ እከሌ ከእከሌ ሳይባል የጋራ ጥቅሙና መብቱ በሕግ የበላይነት ሥር ቢከበርለት፣ ከልዩነቱ ይልቅ አንድነቱ እጅግ በጣም ሰፊና ጥልቅ ነው፡፡

በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ማድረግ የሚገባቸው ልሂቃን ተብዬዎች ደግሞ፣ በሕዝብ ውስጥ ውዥንብር እየፈጠሩ ቀውስ እያባባሱ ይመስላል፡፡ ለዚህ ማሳያው በአገራችን ያሉ መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም በተለያዩ ጊዚያት የተለያዩ ሀሳቦችን እያመጡ አንድነትን ሳይሆን ልዩነትን የመስበክ አይነት አዝማሚያዎች በግልጽ ይስተዋላል። በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ውስጥ በየዕለቱ በሚዋዥቅ አስተያየታቸውና ቅስቀሳቸው መንታ ስብዕና የተላበሱ አክቲቪስቶች በአገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ነው፡፡ ለጋራ አገር የሚጠቅም ሐሳብ አፍላቂዎች መሆን ሲገባቸው፣ በተከመሩ ችግሮች ላይ ተጨማሪ እየፈበረኩ ሕዝብን ውዥንብር ውስጥ እየከተቱ ይገኛሉ፡፡

ህብረ ብሄራዊነት ደግሞ ለአገር አንድነት ችግር እንደማይሆን እንደ ኢትዮጵያ ያሉም አገራት አስረጂ ሆነዋል። ለምሳሌ ህንድ ወደ 21 የሚጠጉ ቋንቋዎች የሚነገሩባት ሃገር ብትሆንም ልዩነታቸውን እንደጥበብ በማድረጋቸው በቅርቡ የተሳካ አገራዊ ምርጫ አድርገዋል። በተመሳሳይ ኔፓል ወደ 123 የሚሆኑ ብሄሮች የገነቧት ሃገር ናት። ኢንዶኔዥያን የፈጠሩ ብሄሮች ከ300 በላይ ቢሆኑም አገራዊ አንድነታቸውን ጠብቀው ይኖራሉ። አፍሪካ አገር እንኳን ሳይቀር ደቡብ አፍሪካ አስራ ሁለት በሚሆኑ ብሄሮች የተፈጠረች ሃገር ነች።  ፓፑዋ ኒው ጊኒ ከ850 ቋንቋ በላይ በሚናገሩ ልዩ ልዩ ብሄሮች ነው የተፈጠረችው።

ከአፍሪካ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታቸውና በኢኮኖሚ እድገታቸው ምሳሌነትን ያተረፉት ጋና እና ቦትስዋና ህብር ናቸው።  በአጠቃላይ በዓለም ላይ እስከ 7 ሺህ የሚደርስ ቋንቋ የሚነገር ሲሆን ይህን ያህል ቋንቋ የሚናገሩ የሰው ልጆች ከሁለት መቶ በሚያንሱ መንግስታት ወይም የፓለቲካ አምድ ስር ተጠቃለው ይኖራሉ። በመሆኑም ህብረ ብሄራዊ መሆናቸው አንድነታቸውን በልዩነት ውስጥ የጸና መሰረት ላይ የጣሉ በመሆናቸው የጎላ ችግር አላጋጠማቸውም።

እናም ኢትዮጵያዊነት ከነፍስና ሥጋ ጋር የተሸመነች ማንነት እንደሆነች በተለያዩ ጊዜያት ምሁራን ያስረዳሉ።የታሪክ ምሁሩ መምህር ታየ ቦጋለ እንደሚገልጹት ይህች አገር አባቶቻቻን ዳዋ ጥሰው፣ ጤዛ  ልሰው፣ ድንጋይ ተንተርሰው፣ ከአንድ ፅዋ ውኃ ተቋድሰው ሉአላዊነቷን አስጠብቀው ቆይተዋል።  በመሆኑም እዚህ ግባ በማይባሉ ምክንያቶች የአገርን ራዕይና ተስፋ የሚያጨናግፉ ተግባራትን አንፈጽም። ብንራብም ብንጠማም ኢትዮጵያዊነታችን ይሻላልና በኢትዮጵያዊነታችን እንዝለቅ ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ በመግለጫቸው አሳስበዋል። እንደ እሳቸው አባባል  የእርስ በርስ ግጭቶችን በወንድማማችነት ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ሰብዓዊ ፍጡር እያሰብንና እየተሳሰብን እናስወግድ። ለጊዜያዊ ሥልጣንና ጥቅም ብለን በወንድማማች ሕዝቦች መካከል የማያባራ ቅራኔና ጥላቻ አንፍጠር፡፡ መገዳደል፣ ማቁሰል፣ በጥላቻ ዓይን መተያየት ትርፍ የሌለው ቢዝነስ ነውና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እናብቃ ሲሉም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ለነገሩ እንኳን በለውጥ ላይ ያለች ሀገር ሌላም ጊዜ ቢሆን ምናልባትም ጥቅመኞች እና የከሰሩ ፖለቲከኞች የአገራችንን ህዝቦች በመከፋፈል ጊዜያዊ ጥቅማቸውን ያሳኩ ቢመስላቸውም ኢትዮጵያን ማንም ከነበረችበት ነቅነቅ እንደማያደርጋት በታሪክ ይታወቃል። በዚህም  ‹አዲስ ወግ›› በሚል ርዕስ ለሦስተኛ ጊዜ ‹‹የሕግ የበላይነት በዴሞክራሲ ሽግግር ሒደት›› በሚል መሪ ቃል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በተካሄደው ውይይት ላይ በድንገት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ባለው ሁኔታ የሚያሰጉ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ኋላ የማይመለስ ዴሞክራሲ መትከል እንችላለን፤›› በማለት ተናግረዋል።

በዚህ መድረክ ላይ በመገኘት አሁን እየታ ባለው ጉልበትና ፖለቲካን ነጣጥሎ ማየት እንደማይቻል የጠቆሙት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር)፣ ዋናው በአገሪቱ የሚታየው ችግር የመንግሥታትን ባህርይ ካለመረዳት የመነጨ ነው ይላሉ፡፡ በዚህ ምክንያት በተፈጠረ ችግር በአገራችን ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ህዝቦች መፈናቀል ምክንያት እንደነበር ችግሩን እንዲያጠና ከተቋቋመው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘ መረጃ ያሳያል።

በጥቅሉ ብዙ ሆነን አንድ በምታደርገን አገራችን ጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲኖር ከተፈለገ ከዘረኝነትና ከራስ ወዳድነት መፅዳት ብቻም ሳይሆን፤ ልዩነትን በሚሰብከው ማንኛውንም ህግጋትና ደምቦችን በማፈራረስ ወደአንድነት በሚያመጡ ህጎች ሊተኩ ይገባል። በመሆኑም በተሳሳተ ትርክት ለዘመናት የተቀነቀኑ ስራዎች የወለደው አክራሪ ብሔርተኝነት ለ21ኛው ክፍለ ዘመን አኗኗር የማይመች ብቻም ሳይሆን አስጊ በመሆኑ በጊዜ ሊኮረኮም ይገባል። በመሆኑም በተዛቡ አመለካከቶች ሳቢያ የሚፈጠሩ ቅሬታዎች ወደ ቅራኔ እያደጉ፣ ለፀፀት የሚዳርጉ እኩይ ድርጊቶች ከመፈጸማቸው በፊት መንግስትም ከዕምነት ተቋማት፣ ከሲቪክ ማህበራት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ጋር በመተባበር የተጀመረውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የበለጠ በማዳበርና ተቋማዊ በማድረግ የኢትዮጵያ አንድነት ላይ መስራት ይገባል መልዕክታችን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም