በመምህራን ላይ የተከሰተው መፈናቀልና የሥራ ስንብት በአስቸኳይ ተጣርቶ ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠው ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በመምህራን ላይ የተከሰተው መፈናቀልና የሥራ ስንብት በአስቸኳይ ተጣርቶ ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠው ተጠየቀ
ጎንደር ግንቦት 23/2011ተከስቶ በነበረው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ምክንያት በመምህራን ላይ የተከሰተው መፈናቀልና የሥራ ስንብት በአስቸኳይ ተጣርቶ ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠው የጎንደር ከተማ መምህራን ጠየቁ፡፡
መምህራኑ “የአካዳሚክ ነጻነት ይከበር፤ ለመምህራን ልዩ ትኩረት ይሰጥ በሚል” በዛሬው ዕለት በከተማው ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡
በሰልፉ ማብቂያ ላይ መምህራኑ በከተማው ከንቲባ ጽህፈት ቤት በመገኘት ያወጡትን ባለ 10 ነጥብ የአቋም መግለጫ በተወካያቸው በኩል አቅርበዋል፡፡
በአቋም መግለጫቸውም በክልሉም ሆነ ከክልሉ ውጪ በሚገኙ መምህራን ላይ በጸጥታ ችግር ምክንያት የተፈናቀሉና የተሰናበቱ መምህራን ጉዳይ በአስቸኳይ ተጣርቶ ዘላቂ ጥቅማቸው የሚከበርበት ሁኔታ እንዲመቻች ጠይቀዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ በ2009 ዓ.ም ለመንግስት ሠራተኞች የተደረገው የደመወዝ ጭማሪ መምህራንን ባለማካተቱ ለዝቅተኛ የደመወዝ እርከን መነሻና ኑሮን ለመቋቋም ከማንችልበት ደረጃ ላይ የደረሰን በመሆኑ የደመወዝ ማስተካከያ ይደረግልን ብለዋል፡፡
የመምህራን ትምህርት ኮሌጅ የመምህራን የትርፍ ሰአት ክፍያ ማነስና 35 ፐርሰንት ታክስ መቆረጥ እንዲሁም በትገበራ ላይ የቆየው የመኖሪያ ቤት አበል ዝቅተኛ በመሆኑ እንዲሻሻል ጠይቀዋል፡፡
መምህራኑ በአቋም መግለጫቸው በግብአት እጥረት ከደረጃ በታች በማስተማር ላይ የሚገኙ የትምህርት ተቋማት ተገቢው ትኩረት እንዲሰጣቸውና ወጥ የሆነ የስልጠና ስርአት በመዘርጋት የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥም ጠይቀዋል።
በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሚያስተምሩ መምህራን በሥራ ላይ በሚገጥማቸው አደጋ የህይወት መድህን ዋስትና እንዲገባላቸውና በኮሌጆቹም የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት መስጫ ክሊኒክ እንዲቋቋም ጥያቄ አቅርበዋል።
የመምህራን ጥቅማጥቅምን ጨምሮ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ አሰጣጥ የአሰራርና የአፈጸጸም ደንቡ እንዲከበር ሲሉም በአቋም መግለጫቸው ላይ አመልክተዋል።
ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል በከተማው የሕብረት ትምህርት ቤት መምህር ደጀን አስፋው “ከ27 ዓመት ወዲህ እኛ መምህራን ለመጀሪያ ጊዜ ጥያቄያችንን በሰላማዊ መንገድ እንድናቀርብ የሰላማዊ ሰልፍ ፈቃድ ማግኘታችን አስደስቶኛል” ብለዋል።
በከተማው የክልል ሩፋኤል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር አበበ ጓንቼ በበኩላቸው “የመምህርነትን ሙያ ከልብ እወዳለሁ፤ መንግስት ለመምህራኑ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ እሻለሁ” ብሏል፡፡
የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ በሪሁን ካሳሁን ለመምህራኑ በሰጡት ምላሽ የመምህራኑ ጥያቄዎች በፌደራልና በክልል ደረጃ ጭምር የሚፈቱና ከተማ አስተዳደሩም የራሱን ድርሻ ወስዶ ምላሽ የሚሰጥባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
“ጥያቄዎቹ ወቅታዊና አግባብ ያላቸው ናቸው” ያሉት ምክትል ከንቲባው፣ የመምህራንን የመኖሪያ ቤት ግንባታ ቦታ ጥያቄ ከተማ አስተዳደሩ በዚህ ዓመት ለመፍታት ባደረገው ጥረት በ33 ማህበራት ለተደራጁ 678 መምህራን ቦታ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ቁጥራቸው አንድ ሺህ የሚጠጉ የመጀመሪያ፣ የሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም የመሰናዶና የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ መምህራን መሳተፋቸው ታውቋል፡፡