ቀጥታ፡

ቦይንግ በ737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች ይቅርታ ጠየቀ

ግንቦት 23/2011 የቦይንግ ኩባንያ ስራ አስፈጻሚ በቦይንግ ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች የተሰማቸውን ሃዘን በመግለጽ በኩባንያው ስም ይቅርታ ጠይቀዋል።

የቦይንግ ኩባንያ ስራ አስፈጻሚ በቦይንግ ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች የተሰማቸውን ሃዘን በመግለጽ በኩባንያው ስም ይቅርታ ጠይቀዋል።

ስራ አስፈጻሚው ዴኒስ ሚዩልበርግ ከሲቢኤስ ቲቪ ጋር ባደረጉት ቆይታ ነው ይቅርታውን በይፋ የጠየቁት።

የቦይንግ ስሪት የሆነው 737 ማክስ 8 አውሮፕላን በኢትዮጵያና ኢንዶኔዥያ በገጠመው ሁለት አደጋ በጠቅላላው የ346 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።

የቦይንግ ኩባንያ እና የአሜሪካ የበረራ ደህንነት መቆጣጠሪያ ቢሮ በአውሮፕላኑ ሶፍትዌር ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት ጥረት እያደረጉ ቢሆንም የኩባንያው ደንበኛ የሆኑ አየር መንገዶች አውሮፕላኑን ከበረራ አግደውታል።

አውሮፕላኑ መቼ ወደ በረራ እንደሚመለስ በግልጽ የተቀመጠ የጊዜ ገደብ የለም።

ዋና ስራ አስፈጻሚው በቃለ ምልልሳቸው አደጋው በኩባንያው ስህተት መፈጠሩን  አምነው፤  “ሶፍትዌሩ ሲዘጋጅ በአግባቡ አልሰራነውም። ኢንጅነሮቻቸን ይህንኑ ደርሰውበታል” ብለዋል።

ዋና ስራ አስፈጻሚው እንዳስታወቁት፤ ኩባንያው በ2017 ላይ በአውሮፕላኑ ላይ የተገጠመው የአደጋ ጊዜ ማስጠንቀቂያ መብራት እንደማይሰራ ቢደርስበትም ለአገሪቱ የአቪየሽን ተቆጣጣሪ ቢሮ ይህንኑ ችግር አላሳወቀም ነበር።

በወቅቱ ችግሩን በተመለከተ መደረግ የነበረበት የጥንቃቄ ተግባር አለመከናወኑንም ገልጸዋል።

በደረሰው አደጋ የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ለተጎጂ ቤተሰቦች  የገለጹት ዋና ስራ  አስፈጻሚው፤ “የአደጋውን መንስኤ በሁሉም አቅጣጫ እያጠናነው የምንገኘው ስህተቱን  ወደ ሌላ አካል ለማስተላለፍ ወይም ጣት ለመቀሰር ሳይሆን የችግሩን  ምንጭ ከመሰረቱ በማጥናት የአውሮፕላኑን ዲዛይን በመቀየር ደህንነቱን አስተማማኝ ለማድረግ ነው” ብለዋል።

የአውሮፕላኑ ችግር ቢቀረፍ እንኳን ደንበኞች መልሰው ለመሳፈር ማመንታታቸው እንደማይቀር ያላቸውን ስጋትም ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።


ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቦይንግ የአውሮፕላኑን ስያሜ እንዲያጤንበት የሰጡትን ምክረ ሀሳብ በተመለከተ ሲናገሩ ጉዳዩ “የስያሜ ችግር ሳይሆን የደህንነት ስጋት ነው” ብለዋል።

የአውሮፕላኑን ስያሜ የምንቀይርበት ምንም ምከንያት የለም በማለት አቋማቸውን አሳውቀዋል።

ቦይንግ 737 ማክስ 8 ከአሜሪካ የአቪየሽን ቁጥጥር ቢሮ ፈቃድ ካገኘ በረራውን በነሃሴ ወር ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም