የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ይካሄዳሉ
ግንቦት 23/2011 የሐበሻ ሰሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ እና ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ።
ነገ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ከጠዋቱ ሶስት ሰአት መከላከያ ከመዳወላቡ ዩንቨርሲቲ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ከነገ በስቲያ እሁድ ሶዶ ላይ የፕሪሚየር ሊጉ መሪ ወላይታ ድቻ ከሙገር ሲሚንቶ ከረፋዱ አራት ሰአት ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ እጅጉን ተጠባቂ ነው።
ወላይታ ድቻ ተጋጣሚውን ሙገር ሲሚንቶ ካሸነፈ ለሁለት ዓመት በተከታታይ የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ መሆኑን ያረጋግጣል።
ሁለቱ ክለቦች ከሁለት ወር በፊት በግብጽ ርዕሰ መዲና ካይሮ በተካሄደው የአፍሪካ የቮሊቦል ክለቦች ውድድር እርስ በእርስ ባደረጉት ጨዋታ ወላይታ ድቻ ሙገር ሲሚንቶን በአምስት የጨዋታ መደብ 3 ለ 2 ማሸነፉ አይዘነጋም።
ሁለቱ ክለቦች በአፍሪካ መድረክ ያደረጉት ጠንካራ ፉክክር በአፍሪካ መገናኛ ብዙሃን አድናቆት ያስቸራቸው ሲሆን በአህጉር ደረጃ ያሳዩትን ፉክክር በፕሪሚየር ሊጉም ጨዋታ ይደግሙታል ተብሎ ይጠበቃል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር የፕሪሚየር ሊግ አራተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ተገናኝተው ወላይታ ድቻ ሙገር ሲሚንቶን በአራት የጨዋታ መደብ 3 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
በመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ወላይታ ድቻ ሙገርን 42 ለ 40 ያሸነፈበት ነጥብ በኢትዮጵያ የቮሊቦል ታሪክ በአንድ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከፍተኛ ነጥብ የተመዘገበበትም እንደነበር አይዘነጋም።
ጨዋታው ከ2 ሰዓት በላይ የፈጀና ከፍተኛ የተመልካች ቁጥር የተገኘበትም ነበር።
እሁድ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ከቀኑ ስምንት ሰአት ላይ አዲስ አበባ ፖሊስ ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ማክሰኞ ግንቦት 27 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ከጠዋቱ ሶስት አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ከጣና ባህርዳር ጋር የሚጫወቱ ይሆናል።
የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ወላይታ ድቻ በ34 ነጥብ ሲመራ፣ መዳወላቡ ዩንቨርሲቲ በ29 ሙገር ሲሚንቶ በ23 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
አዲስ አበባ ውሃና ፋሳሽ በሁለት ነጥብ የመጨረሻውን ስምንተኛ ደረጃን ይዟል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ይካሄዳሉ።
ነገ ጎንደር ላይ ከጠዋቱ ሶስት ሰአት ጎንደር ከተማ ከቡታጅራ ከተማ ዱራሜ ላይ ከምባታ ዱራሜ ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች ከረፋዱ አምስት ሰአት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ፌደራል ፖሊስ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ መቐለ ላይ መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከመከላከያ በተመሳሳይ ከጠዋቱ ሶስት ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ በፎርፌ በማግኘቱ የሁለት ነጥብና የ10 ለ 0 አሸናፊ መሆኑን ከኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ድሬዳዋ በፋይናንስ ችግር ከውድድሩ መውጣቱ ይታወቃል።
በቀጣይ ሳምንታት የውድድር መርሃ ግብር ከድሬዳዋ ከተማ ሊጫወቱ የነበሩ ክለቦች በውድድሩ ደንብ መሰረት የፎርፌ ውጤት እንደሚያገኙ ፌዴሬሽኑ ገልጿል።
የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በ28 ነጥብ ሲመራ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ22 መቐለ ሰብዓ እንደርታ በ20 ነጥብ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።