የእንቦጭ አረም አፋጣኝ መፍትሄ ካልተሰጠው ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ስጋት ይሆናል - ኢዜአ አማርኛ
የእንቦጭ አረም አፋጣኝ መፍትሄ ካልተሰጠው ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ስጋት ይሆናል
ግንቦት 23/2011 የእንቦጭ አረም በአገሪቷ እያደረሰ ያለው ጉዳት በጊዜ ካልተገታና መፍትሄ ካልተበጀለት የታላቁ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች የውሃ አካላትን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጎዳ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ገለጸ።
አረሙ በአገር ደረጃ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል የሚያስችል ስርዓት ባለመዘርጋቱና ችግሩን የሚከላከል ተቋም ባለመኖሩ የጉዳቱ መጠን እየሰፋና እየጨመረ መምጣቱን አክሏል።
ዋና ኦዲተር የ2010 ዓ.ም ክዋኔ ኦዲት ሪፖርትን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት ''የእንቦጭ አረም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል የሚያስችል ስራ የሚሰራ ተቋም የለም'' ብሏል።
በመሆኑም መስሪያ ቤቱ አረሙ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል የሚደረገውን እንቅስቃሴ ኦዲት ለማድረግ መቸገሩን ጠቅሷል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት የብዝሃ ህይወት ሃብትን ከውጭ በሚገቡ ወራሪ መጤ ዝርያዎች እንዳይበከሉና ጥፋት እንዳይደርስባቸው ቁጥጥርና ክትትል እንዲያደርግ በአዋጅ ተደንግጓል።
ይሁንና ኢንስቲትዩቱ የእንቦጭ አረምን በተመለከተ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ብዙ ጥናትና ምርምር እያደረጉ ነው በሚል በህግ የተሰጠውን ስራ እየሰራ አይደለም ።
የቀድሞ የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴርም አረሙን ለመከላከል፣ ለመቀነስ፣ ምንጩንና የስርጭቱን መጠን ለይቶ በሃይቆችና በወንዞች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ስራ ባለመስራቱ በወንዞቹና ሃይቆቹ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖና ጉዳት እየደረሰ ይገኛል።
ስለሆነም የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ በክልል ደረጃ የሚደረጉ ጥናቶች ቢኖሩም በአገር አቀፍ ደረጃ የተሟላ ጥናት በማድረግ አረሙ የሚፈጠርበትን ሁኔታ፣ ምንጩንና የስርጭቱን መጠን በማወቅ ለመከላከልና የጉዳት መጠኑን ለመቀነስና ለመቆጣጠር የሚያስችል በጥናት የተደገፈ የተቀናጀ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ጥረት እየተደረገ አይደለም።
በዚህም የእንቦጭ አረም እያደረሰ ያለው ችግር ከጣና ሀይቅ በተጨማሪ በዝዋይና በአባያ ሐይቆች እንዲሁም በባሮና በሌሎች ወንዞች ላይ እየታየና እየተስፋፋና መጥቷል።
የችግሩ ስፋትና ግዝፈት ግንዛቤ አግኝቶ አስፈላጊው የተቀናጀ ስትራቴጂ ተነድፎና ተገቢው ሃብት ተመድቦለት በአስቸኳይ ካልተተገበረና ካልተሰራ የታላቁን የህዳሴ ግድብ ጨምሮ በሀይቆችና በወንዞች ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ አደጋ በመሆኑ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ አሳስበዋል።