የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የገንዘብ እጥረት እንደገጠመው ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የገንዘብ እጥረት እንደገጠመው ገለጸ
አደስ አባበ ግንቦት 22/2011 የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በገጠመው የገንዘብ እጥረት ምክንያት በግንቦት ወር ለሰራተኞች ደመወዝ የሚከፈል በቂ ገንዘብ የለውም።
የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እንድሪስ እንደገለጹት ካለፈው የመጂሊሱ አመራር ሃላፊነት ከተረከቡ በኋላ በምክር ቤቱ የባንክ አካውንት የተገኘው አንድ ሚሊዮን ብር ብቻ ነው።
ይህ ደግሞ ለሰራተኞች ወርሃዊ የደሞዝ ክፍያ እንኳን ለመሸፈን በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል።
ለሰራተኞች ደሞዝ 3 ሚሊዮን ብር ወርሃዊ ክፍያ እንደሚያስፈልግ የገለጹት ሃጂ ዑመር አሁን ያለው ገንዘብ ለግንቦት ወር ክፍያ እንኳን መሸፈን አይችልም።
በመሆኑም ችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እስከሚበጅለት ድርስ ህዝበ ሙስሊሙና ባለሃብቶች፣ እንዲሁም ተቋማት የቻሉትን ሁሉ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ምክር ቤቱ ከተቋቋመ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረና የተለያዩ የገቢ ምንጮች ያሉት ቢሆንም አሁን በተጨባጭ የተገኘው ገንዘብ ግን እጂግ በጣም አነስተኛ መሆኑ ነው የተነገረው።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ምክር ቤቱ ከሃጂና ኡምራ ጉዞ ከሚያገኘው ገቢ በተጨማሪ ከቤት ኪራይ ብቻ በዓመት 70 ሚሊዮን ብር ይሰበስባል።
"ይሁን እንጂ አሁን በተጨባጭ የተገኘው ገንዘብ የገቢውን መጠን ያላገናዘበና ለሰራተኞች እንኳን የአንድ ወር ደሞዝ መሸፈን የማይችል በመሆኑ ድርጊቱ ሁላችንንም አሳዝኗል" ብለዋል ሐጂ ዑመር።
በአሁኑ ጊዜ የሰራተኞችን የደሞዝ ክፍያና የስራ ማስኬጃ ተጨምሮበት በወር 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል።
ይሁን እንጂ አዲሱ አመራር ከቀድሞው የተረከበው በተራቆተ ካዝና የእለት ስራን ለማከናወን እንኳን የገንዘብ ችግር እንቅፋት ሆኖበታል።
"በመሆኑም በአደባባይ እርዳታ ለመለመን ተገድጃለሁ" ያሉት ቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እንድሪስ በጎ ምላሽ እንደሚያገኙም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ለሚፈልጉ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጦር ሃይሎች ቅርንጫፍ የሂሳብ ቁጥር 1000024736408 ወይም በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ሂሳብ ቁጥር 137526 ማስገባት እንደሚችሉ ገልፀዋል።