አገራዊ አንድነትን በማጠናከር የሰላም ስጋቶችን በጋራ መከላከል እንደሚገባ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
አገራዊ አንድነትን በማጠናከር የሰላም ስጋቶችን በጋራ መከላከል እንደሚገባ ተጠቆመ
ግንቦት 22/ 2011 የህብረተሰቡን የቆዩ የመቻቻልና የመከባበር እሴቶች በማጎልበትና አገራዊ አንድነትን በማጠናከር የሰላም ስጋቶችን በጋራ መከላከል እንደሚገባ ተጠቆመ።
የሉሲን ወደ ጋምቤላ ክልል መምጣት ተከትሎ በጋምቤላ ከተማ የሰላም እሴቶችን በማጠናከር ዘላቂ ልማትን መገንባት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ዛሬ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉት በህብረተሰቡ ዘንድ የቆዩ የመቻቻል፣ የመከባበር፣ የአብሮነትና ሌሎች መልካም እሴቶችን በማጎልበት ለአገራዊ አንድነት ሁሉም በጋራ መስራት ይኖርበታል።
በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ሰላም እንዳይኖርና በህብረተሰቡ ዘንድ የነበረውን የአንድነት ስሜት የሚሸረሽሩ ግጭቶች እንዲፈጠሩ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
እነዚህን አካላት በጋራ መከላከልና ለህግ አሳልፎ መስጠት የሁሉም ትኩረት ሊሆን እንደሚገባም ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ዶክተር ሎው ኡቡፕ በሰጡት አስተያየት እንዳሉት በክልሉ ብሎም በአገሪቱ ሰላምና ዘላቂ ልማት እንዲኖር እያንዳንዱ ዜጋ በግለሰብ ደረጃ ለሰላም ዘብ መቆም ይኖርበታል፡፡
"ሰላምን በግለሰብ ደረጃ ማስፈን ከቻልን ወደ ቤተሰብ፣ ማህብረሰብና ህዝብ ማሳደግ እንችላለን" ያሉት ዶክተር ሎው፣ በተለይ አገራዊ እንድነት እንዲመጣ ሁሉም ለሰላም ስጋት የሚፈጥሩ አካላትን በጋራ መከላከል እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
በአገሪቱ ብሎም በክልሉ የተጀመረውን ለውጥ እውን ለማድረግና የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሰላምን ማስፈን ዋነኛ መሳሪያ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ኩዊች ዊው ናቸው፡፡
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ የሰላም ችግሮችን ለመፍታት የጋራ ውይይቶችን በማድረግ በህዝቡ ዘንድ የነበረውን ጠንካራ የመቻቻል፣ የመከባበርና የአንድነት እሴቶች መመለስ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
ለዚህም የሃይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ስራ መጠናከር እንዳለበት ነው የጠቆሙት ፡፡
እንደ አቶ ኩዊች ገለጻ መንግስትም ስለሰላም በመድረክ ከመግለጽ ባለፈ ታች ወደ ህብረተሰቡ ወርዶ ተግባራዊ ስራዎችን መስራት ይኖርበታል።
የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ ኃይለማሪያም ተክለማሪያም በበኩላቸው “የሉሲ ቅሬት አካል ወደ ክልሉ መምጣቱ ሰላምን ከመስበክ ባለፈ ሁሉም የሰው ዘር መገኛው አንድ ግንድ መሆኑን ማሳያ ነው” ብለዋል፡፡
በመሆኑም ሁሉም የሰው ልጅ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቀለም ቢለያይም በሰውነቱ አንድ መሆኑን በማየት ለአገራዊ አንድነትና ዘብ ሊቆም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
“ይህንን ለማሳካት ለሰላም እንቅፋት የሚሆኑ አካላትን ሁሉም በጋራ መከላከል ይገባል” ብለዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው “በክልሉ የህዝቡን አንድነት በማጎልበት ለአገሪቱ ሰላም የምናደርገውን ጥረት አጠናክረን እንቀጥላለን” ብለዋል፡፡
ይህን ማሳካት የሚቻለው እያንዳንዱ ዜጋ እኔና የእኔ ከሚል ጠበብ ያለ አስተሳሰብ ሲወጣ ብቻ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም የክልሉ ብሎም የአገሪቱ ህዝብ ከዚህ አስተሳሰብ በመላቀቅ ለአገራዊ አንድነት የሚያደርገውን ጥረት ይበልጥ ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
መንግስት የዜጎችን መብት በማስከበር ለክልሉና ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንደሚያጠናክርም ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ላይ "የኢትዮጵያ ታሪክ ትናንትና ዛሬ እንዲሁም የሰላም እሴቶች ግንባታና ዘላቂ ሰላም" በሚሉ ርዕሰ ጉዳይች በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡