የጋራ ባለታሪክ ህዝብ በጋራ ታሪኩ ለምን ይነታረካል? - ኢዜአ አማርኛ
የጋራ ባለታሪክ ህዝብ በጋራ ታሪኩ ለምን ይነታረካል?
አዲስ አበባ ግንቦት 22/2011 ታሪክ የነገን ትውልድ ታሳቢ ያደረገ ሚዛናዊ፣ የጋራ እሴትና ታሪኮች ላይ ማተኮር እንደሚገባ የመስኩ ተመራማሪዎች አመለከቱ።
እንደ ድርና ማግ የተሳሰረ የጋራ ታሪኮችና እሴቶችን በማጉላት የሁሉም የምትሆን ኢትዮጵያ መፍጠር ለመንግስት፣ ለምሁራንና ለሃይማኖት ተቋማት የጋራ ፕሮጀክት ሊሆን እንደሚገባም ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ህዝቦቿ ለዘመናት በክፉም፣ በመልካምም የታሪክ ገጾች በህብርት፣ በአብሮነት የዘለቁባት፣ ለብዙ ሺ ዓመታት በነጻነት የኖረች ታሪካዊና ጥንታዊት አገር ብትሆንም በጋራ ታሪክ ላይ ብዥታዎችና አለመግባባቶች ተበራክተው መቀጠላቸውን በርካታ ሰዎች ያነሳሉ።
ለመሆኑ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ታሪክና እሴት ምንድን ነው? ታሪክ ለንትርክ መንስኤነቱስ ከምን የመነጨ ነው? በሚለው ጉዳይ ላይ ኢዜአ የዘርፉን ምሁራን አናግሯል።
አቶ ታዬ ቦጋለ በተለያዩ ትምህርት ተቋማት ለ30 ዓመታት በታሪክ መምህርነትና ተመራማሪነት ያገለገሉ ሲሆን፤ "መራራ እውነት በኢትዮጵያ ታሪክ" የተሰኘ በታሪክ አጻጻፍና በኢትዮጵያ ታሪክ ትንታኔ ላይ ያጠነጠነ መጽሃፍ በዚህ ሳምንት አሳትመዋል።
-
አቶ ታዬ ቦጋለ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ
የአንድ አገር ታሪክ የሁሉም በብሄር ብሔረሰብ "የጋራ ታሪክ ነው" የሚሉት አቶ ታዬ፤ ግሪክና አሜሪካዊያን ለአብነት በማንሳት በአገራቱ በሚገኙ ግዛቶች የተደረገ የትኛውም ኹነት የጋራ ታሪክ እንጂ የተናጠል እንዳይደለ ያወሳሉ።
በኢትዮጵያም ከቅድመ አክሱም ጀምሮ በሁሉም አቅጣጫ የሚታየው ማህበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና አካባቢያዊ የታሪክ ኹነትና የአገር መንግስት ምስረታ ሂደት የጋራ ታሪክ መሆኑን ነው አጽንኦት የሚሰጡት።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ስነ ህዝብ ጥናት ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰርና የምርምራቸውን ትኩረት በማህበራዊና ብዝሃንነት ጉዳዮች ያደረጉት ዶክተር ከይረዲን ተዘራ፣ የበርካታ ህዝቦች ባለቤቷ ኢትዮጵያ በርካታ ያዳበሯቸው የጋራ እሴቶችእንዳሏቸው ይገልጻሉ።
-
ዶ/ር ከይረዲን ተዘራ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ስነ ህዝብ ጥናት
ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር
በአገር መንግስት ምስረታና ኢትዮጵያ እንደ ኢትዮጵያ ተጠብቃ የመቆየቷ ታሪክ የሁሉም ህዝቦች ጥረት ውጤት መሆኑን፣ በታሪክ፣ በባህልም፣ በኢኮኖሚም መስኮች የሚገለጽ ማህበራዊ ትስስርና አብሮነት የጋርዮሽ መገለጫዎች ናቸው።
‘ድርና ማግ’ የመጣንበት መንገድ፣ ተስፋና ስጋቶቻችን’ በሚል በኢትዮጵያዊያን የጋራ ታሪክና እሴቶች ላይ ያተኮረ መጽሃፍ ከሰሞኑ ያሰመረቁት አቶ ብሩክ ከድር ኢትዮጵያዊያን ድርና ማግ ያደረጉ የጋራ ታሪኮችና እሴቶች ባለቤት መሆናቸውን ይሰማማሉ።
-
አቶ ብሩክ ከድር
የመጣንበት መንገድ ክፉም ፣በጎም ገጽታዎች እንዳሉት የሚገልጹት አቶ ብሩክ፤ በልሂቃን የተጻፉ ታሪኮች ግን ከሚያግባቡት ይልቅ ከፋፋይ ታሪኮች ገዝፈው እንደሚስተጋቡ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ አጻጻፍ ሂደት ሚዛኑን የጠበቀ አካታች የታሪክ ይዘት አለመኖሩንም በማንሳት፣ ለዚህ በአንድ በኩል የታሪክ ጠባሳዎችን መዘንጋት፣ በሌላ በኩል ጭቆናን ብቻ በማሰብ የሚቆዝሙ ሊሂቃን መበራከታቸውን እንደምክንያት ያነሳሉ።
የጋራ ታሪክና እሴት ባለቤት ህዝቦች መካከል የሚፈጠረው የታሪክ አለመግባባትና ንትርክ የልሂቃኑ በራሳችው የአስተሳሰብ በረት መወሸቅና ታሪክን ወደራስ ብሔር የመውሰድ አባዜ መሆኑን አቶ ታዬ ቦጋለ ያብራራሉ።
በሌላ በኩል ታሪክ በጠለቀና በመጠቀ አካሄድ የሚጻፍ ቢሆንም መንግስት በታሪክ ውስጥ ያለው ጣልቃ ገብነት ወይም አካዳሚያዊ ነጻነት አለመኖር የጋራ ታሪክና እሴት እንዳይጎላ አድርጓልም በማለት ይገልጻሉ።
"ታሪክ በካድሬ ከተጻፈ የህዝብ ታሪክ ሳይሆን ፖለቲካ ነው" የሚሉት አቶ ታዬ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ መምከን አንዱ ችግሩ ፖለቲከኞች መንግስት በሚመቸው ልክ እንዲሰፋ ማድረጉ ነው የሚል መሟገቻ ሀሳብ አላቸው።
ታሪክ ከተጠላ ዋጋ እንደሌለው በመግለጽም በንግድ፣ በጦርነት ለዘመናት ተጋምዶ የመጣን የአብሮነት ታሪክና እሴት ያለውን ህዝብ መከፋፈል እንደማይገባ ገልጸዋል።
ታሪክ ትውልድ ተሻጋሪ አወንታዊና አሉታዊ ተጽዕኖ ያለው መሆኑን ተረድቶ ታሪክ እንደማይጻፍ ገልጸው፤ ባለፉት አስርት ዓመታትም ህዝብ ከህዝብ እንዲጋጭ ከፋፋይ ታሪክ ሲስተጋባ እንደነበር አብራርተዋል።
ታሪክ ሲጻፍ መጭውን ትውልድ የሚያጨቃጭቅና የሚያባላ ሳይሆን ትውልድን የሚያስብ የታሪክ ዓላማን መሰረት ያደረገ መሆን እንደሚገባ የሚገልጹት ምሁራኑ፣ በሂደቱም የታሪክ የህግ፣ የማህበራዊ ሳይንስ፣ የስነ ልቦና ምሁራን፣ ማሳተፍና ሚዛናዊነቱን መመዘን እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኢትዮጵዊያን የደመቁ የጋራ የታሪክ ሰበዞች እንዷላችው ጠቁመው፤ ከጦርነት ፖለቲካ ባሻገር ምጣኔ ሀብታዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ማህበራዊ ታሪክን ያቀፈ አካታች ታሪክ መጻፍ እንደሚገባ ነው ያስረዱት።
ምሁራን ከማወያየት፣ ህዝቡንና የማህበረሰብ ሊሂቃንን ከማሳተፍ በተጨማሪ፣ ትውልድ የሚያባላ፣ ህዝብን ከህዝብ ከሚያናክስ፣ ታሪክን ከሚያራክስ፣ አገርን ከሚያዋርድ ነገር ይልቅ ኢትዮጵያዊያን በጋራ የቆሙባቸውን እሴቶችና ምሰሶዎቻቸውን በደንብ አድርጎ ማሳየት እንደሚገባ አብራርተዋል።
ሀቀኛ የታሪክ ትርክት ለመጻፍ መፍትሄው ተቋማዊ ምላሽ የሚጠይቅና በሁለት ጠርዞች መካከል ያለውን ማቀራረብ፣ ከትናንት መማርና አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
የታሪክ ምሁራን የ21ኛው ክፍለ ዘመንን የሚዋጅ ሚዛናዊ አስተሳስብ መያዝ እንደሚገባቸው፤ መንግስትም ከታሪክ ላይ እጁን መሰብሰብ እንዳለበትም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያዊያን ያለፉበት መንገድ ክፉ ብቻ ሳይሆን በጎ ገጽታ እንደሆነ ገልጸው፤ ምሁራንም ሀቀኛ የታሪክ አጻጻፍን ማዳበር፣ የህዝቦች የጋራ እሴቶችን ማጉላት እንደሚጠበቅባቸው ነው የሚገልጹት።
የህዝቡን የጋራ እሴቶችና ታሪኮችን በማጉላት እንዲሁም የጋራ ተስፋዎችን በማሳየት ለሁሉም የምትሆን ኢትዮጵያ መፍጠር ለመንግስት፣ ለምሁራን፣ ለሃይማኖት ተቋማት የጋራ ፕሮጀክት መሆኑን ነው ያከሉት።