ዩኒቨርሲቲው ከ60 በላይ የምርምር ውጤቶችን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ማድረጉን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው ከ60 በላይ የምርምር ውጤቶችን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ማድረጉን አስታወቀ
ጎንደር ግንቦት22/2011ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከ60 በላይ የምርምርና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶችን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
በሀገሪቱ የሚገኙ 22 ዩኒቨርሲቲዎች የተሳተፉበት ሀገር አቀፍ የቴክኖሎጂ ጉባኤ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ተካሂዷል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መስፍን እንደተናገሩት ባለፉት አራት ዓመታት በተቋሙ ተመራማሪዎች ጥናት የተደረገባቸው 30 የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶች ወደ ተጠቃሚዎች ተደራሽ ተደርገዋል፡፡
በተጨማሪም 32 የቴክኖሎጂ ሽግግር ምርምር ፕሮጀክቶችን ለቢዝነስ ኢንተርፕራይዞችና ለኢንዱስትሪዎች ተደራሽ በማድረግ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማሳለጥ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ለአብነት ያህል በግብርናው ዘርፍ በሽታንና ድርቅን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የሰብል ዝርያዎችን ጨምሮ ዘመናዊ የጤፍ መዝሪያ ማሽን በምርምር በማፍለቅ ወደ ተጠቃሚዎች ተደራሽ ማድረግ ተችሏል፡፡
“በቴክኖሎጂው ዘርፍም ያለቁ የላፕቶፕ ባትሪዎች ዳግም እንዲያገለግሉ ከማድረግ ጀምሮ በንፋስ ኃይል የሚሰራ የጉድጓድ ውሃ ማውጫ ፓንፕ ተሰርተው ለአገልግሎት መብቃታቸው ይጠቀሳሉ ብለዋል፡፡
ከወዳደቁ ፕላስቲኮች 6 አይነት የግድግዳ ቀለም የማምረት ቴክኖሎጂን ጨምሮ ለቤተ-ሙከራ ስራ የሚውል ሰልፈሪክ አሲድ ጅብራ ከተባለ ተክል በምርምር ማፍለቅ መቻሉንም ነው አቶ ሰለሞን የተናገሩት፡፡
በምርምሩ ከተሰሩ ስራዎች መካከል የእምቦጭ አረም መሰብሰቢያ ማሽን እና ከእምቦጭ አረም ነዳጅን ማምረት የሚያስችል የቴክኖሎጂ ግኝት ላቅ ያሉ ተጠቃሽ የፈጠራ ውጤቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
“ዩኒቨርሲቲው በቴክኖሎጂ ማፍለቅ ዘርፍ ካከናወናቸው ስራዎች መካከል 11ዱ ከኢትዮጵያ እምሮአዊ ንብረት ጽህፈት የባለቤትነት መብት አግኝተዋል” ብለዋል፡፡
“ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት ለጥናትና ምርምር ፕሮጀክቶች ከ138 ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ ሥራ ላይ እንዲውል አድርጓል” ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ ናቸው፡፡
እንደፕሮፌሰር መርሻ ገለጻ በተቋሙ የጥናትና ምርምር ሥራዎች በጥራትም በቁጥርም ጨምረዋል።
ለእዚህም በተያዘው ዓመት ብቻ 170 የምርምር ፕሮጀክቶች ተካሂደዋል፤ ከ600 በላይ መምህራኖችም ተሳታፊ መሆናቸውን ነው የገለጹት
ባላፉት ተከታታይ ዓመታት በመቶዎች የሚቆጠሩ የዩኒቨርሲቲው የምርምር ውጤቶች አለም አቀፍ እውቅናና ተቀባይነት ባላቸው ጆርናሎች ለህትመት መብቃታቸውንም ተናግረዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን በበኩላቸው ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት የምርምርና የቴክኖሎጂ ስራዎች ወሳኝ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
“ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራ ጎን ለጎን ለጥናትና ምርምር ሥራዎች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው” ያሉት ፕሬዚዳንቱ በዓለም አቀፍ ደረጃም በምርምሩ ዘርፍ ከውጪ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች ግንኙነት መፍጠሩን አመልክተዋል።
ለሁለት ቀናት በቆየው ሀገር አቀፍ ጉባኤ ላይ ተመራማሪዎችና ጥሪ ተደረገላቸው ምሁራን የተሳተፉ ሲሆን 36 የምርምር ውጤቶችም ቀርበው ውይይትና የልምድ ልውውጥ ተደርጎባቸዋል፡፡