የኢትዮጵያ እስልምና ምክር ቤት ከፍተኛ የበጀት ችግር እንደገጠመው ገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እስልምና ምክር ቤት ከፍተኛ የበጀት ችግር እንደገጠመው ገለፀ
አዲስ አበባ ግንቦት 22/2011የኢትዮጵያ እስልምና ምክር ቤት ከፍተኛ የሆነ የበጀት እጥረት እንደገጠመው የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ቀዳሚ ሙፍቲህ ሀጂ ዑመር ኢድሪስ ገለፁ።
የግንቦት ወር የሰራተኛ ደምወዝ ለመክፈል የሚያስችል ገንዘብ እንኳ እንደሌለው ነው ሐጂ ዑመር የተናገሩት።
በቅርቡ በአዲስ መልክ ስልጣኑን የተረከበው ምክር ቤቱ በአሁኑ ወቅት በካዝናው ውስጥ ያገኘው አጠቃላይ ገንዘብ አንድ ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑን ሐጂ ዑመር ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ይህ ደግሞ የአንድ ወር የሰራተኞችን ደሞዝ ለመክፈል እንኳ የሚበቃ አይደለም ያሉት ፕሬዚዳንቱ የምክር ቤቱ ሰራተኞች አጠቃላይ ወርሃዊ ደምወዝ ሶስት ሚሊዮን ብር መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ተቋሙ እየተጠናቀቀ ላለው የግንቦት ወር የሰራተኞች ደምወዝ የሚከፍለው ገንዘብ እንደሌለው አመልክተዋል።
በአገር ውስጥ ያለውም ሆነ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ህዝበ ሙስሊም ይህንን የገንዘብ ችግር ለማቃለል የሚቻለውን ድጋፍ እንዲያደርግ ሐጂ ዑመር ጥሪ አቅርበዋል።