የሀገር ባህል ልብሶች ባህላዊ ይዘታቸው እንዳይጠፋ በዘፈቀደ መሰራት የለባቸውም--አስተያየት ሰጪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር ባህል ልብሶች ባህላዊ ይዘታቸው እንዳይጠፋ በዘፈቀደ መሰራት የለባቸውም--አስተያየት ሰጪዎች
ግንቦት 21/2011 የሀገር ባህል ልብሶች ባህላዊ ይዘታቸው እንዳይጠፋ እንደማንኛውም ልብስ በዘፈቀደ መሰራት እንደሌለባቸው አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በበኩሉ የአልባሳቱን እሴትነት እንዳይሸረሸር የሚያስችል ህግና ደንብ አለመኖሩ አስቸጋሪ አድርጎት እንደቆየ ገልጿል ፡፡
በአዲስ አበባ ጉዳዩን አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የስተያየት ሰጭዎች እንደሚሉት ባህላዊ አልባሳትን ከተለመደው ውጭ በተለየ ዲዛይን መስራት ነባሩ ባህላዊ እሴት እንዲሸረሸር እያደረገ ነው፡፡
ከአስተያት ሰጭዎቹ መካከል አቶ ደነቀው ቢራራ እንደሚሉት ባህላዊ ልብስ ከሌሎች አልባሳት የተለየ ክብር ስላለው እንደማንኛውም ልብስ በዘፈቀደ መሰራት የለበትም ብለዋል፡፡
ባህላዊ ልብሶቻች ከወግ፣ልማድና ባህል ጋር ቁርኝት ስላላቸው ከልብስነት ባለፍ የማንነት መገለጫዎች በመሆናቸው ተንከባክቦ መያዝ ይገባል ነው ያሉት፡፡
“እኛ ያላከበርነውን ሌላ ሊያከብርልን አይችልም፣ መንከባከብና መጠበቅ ያለብን እኛ እራሳች ነን” ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ፋንታነሽ ድንቁ ናቸው ፡፡
ክብረ በዓላትን ከባህል ልብሶች ነጥሎ ማየት አይቻልም የሚሉት ወይዘሮ ፋንታነሽ በተገቢው ሁኔታ ልንከባከባቸው ይገባል ብለዋል፡፡
በተለይ የሴቶች ባህላዊ ቀሚስ ላይ ወጣ ያለ አስራር እንደሚስታዋል ጠቁመው ከነባሩ ባህላዊ አለባበስ ጋር እንደሚጋጭ ይናገራሉ፡፡
በባህል ልብስ የንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ ስንታየሁ ብረሃኑ እንዳሉት ነባሩ የባህል ልብስ አሰራር የበለጠ ውበት ሲኖራቸውና በተለያየ ዲዛይን መሰራት ለደንበኞች እንደፍላጎታቸው እንድያገኙ እድል ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡
ከመጠንና ከቅርጽ በስተቀር የአሰራር ሂደቱንና የሚሰራበት ግብአት ተመሳሳይ ስለሆን በነበሩ አሰራር ላይ ብዙም ተጽእኖ አያሳድርም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አጫጭር የባህል ቀሚሶች ለጉብኝት በሚመጡ የውጭ ዜጎችን ፍላጎት የሚሰሩ በመሆኑ እነሱን ታሳቢ በማድረግ እንደሚሰራ የተናገሩት በባህላዊ የልብስ ስፌትና ዲዛይን ስራ የተሰማሩት አቶ ስንታየሁ ገብረሚካል ናቸው ፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በበኩሉ የአልባሳቱን እሴት እንዳይሸረሸር ለማስጠበቅ የሚያስችል ህግና ደንብ አለመኖሩ ችግሩን ለመከላከል አስቸጋሪ አድርጎት እንደቆየ ተናግሯል፡፡
በሚኒስቴሩ የባህል እንዱስትሪ ልማትና ትብብር ተቋማትና ሙያተኞች ዳይሬክቶሬት ባለሙያው አቶ ተፈሪ ተክሉ እንደጠቀሱት ችግሩን ለመከላከል የባህል ልማት ስትራቴጂ ሰነድ እየተዘጋጀ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በዝግጅት ላይ ያለው ሰነድ ሲጸድቅ የግለሰቦችን የፈጠራ መብት እንዲሁም በአለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን የባለቤትነት መብት ለማስጠበቅ እንደሚያስችል ባለሞያው አመላክተዋል፡፡
ባለሞያው እንዳሉት በጥናት እስካልተረጋገጠ ድረስ አዳዲስ ፈጠራዎችና ዲዛይኖች በነባሩ የባህል እሴቶች ላይ ጫና እያሳደረ ነው ለማለት አያስደፍሩም ነው ያሉት፡፡
በባህላዊ አልባሳት ላይ የተጋረጡ ችግሮችን ለመከላከል አስቸጋሪ ከሚያደርጉ ጉዳዮች መካከል ባህላዊ አልባሳት የህዝብ የወል ሃብት በመሆናቸው በባለቤትነት የሚቆጣጠር አካል አለመኖሩ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በመሆኑም ይላሉ አቶ ተፈሪ ባህላዊ አልባሳት እሴትነታቸውን እንዳያጡ በቀዳሚነትና በተቆርቋሪነት መጠበቅ ያለበት ህብረተሰቡ ነው ብለዋል፡፡
በሚኒስትር ደረጃ አለማቀፋዊነት በነባር ባህል ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን ያልሸሸጉት ባለሞያው ፤መጤ ባህሎችን ለመከላከል ስትራቴጂ ተነድፎ እየተሰራ እንደሚገጥ ተናግረዋል፡፡