በቱሪዝም ዘርፍ ብቁ ባለሙያዎችን ማፍራት ለዘርፉ ልማት ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
በቱሪዝም ዘርፍ ብቁ ባለሙያዎችን ማፍራት ለዘርፉ ልማት ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ
አዲስ አበባ ግንቦት 21/2011በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በቂ እውቀትና ክህሎት ያላቸውን ባለሙያዎች ማፍራት ለአገሪቷ ኢኮኖሚያዊ እድገት ወሳኝ መሆኑን የኢትዮጵያ ሆቴልና ቱሪዝም ስራ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሆቴልና ቱሪዝም ስራ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የተቋቋመበትን 50ኛ አመት በዓል ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባና ቢሾፍቱ የሚገኙ ታሪካዊ፣ ጥንታዊና ዘመናዊ ሆቴሎችን ጎብኝት አድርጓል።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው ጣይቱ ሆቴልን ጨምሮ ራስ ሆቴል፣ በቢሾፍቱ የሚገኙት የኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት፣ ኩሪፍቱና ፒራሚድ ሆቴል ተጎብኝተዋል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ የአገሪቷን እምቅ ሀብቶች በአግባቡ ለማስተዋወቅ በእውቀት፣ በክህሎት፣ በቋንቋ፣ በስነ- ምግባር፣ በእንግዳ አቀባበልና በመልካም መስድተንግዶ ብቁ ባለሙያዎችን በብዛት ማፍራት ያስፈልጋል።
ኢንስቲትዩቱ በሆቴልና ቱሪዝም ሴክተር ባለሙያዎችን በማሰልጠንና ብቁ በማድረግ ረገድ ለዘርፉ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ፍላጎት ያላቸውን በማሰልጠን አካባቢያቸውን እንዲያግዙ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዘርፉ ተወዳዳሪና ከኢንዱስትሪው ፍላጎት ጋር የሚጣጣሙ እውቀትና ክህሎትን ያዳበሩ ባለሙያዎችን ለማብቃትና የአገሪቱንም የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ተቋሙን አሁን ካለበት ቁመና ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስና ወደ አለም አቀፍ ኢኒስቲትዩትነት እንዲሸጋገርም እየተሰራ ይገኛል።
ሙያተኞችን ከማሰልጠን ባሻገር የስራ እድል እንዲያገኙ ለማመቻቸትም ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
በዚህ አመት በቀንና በማታ መርሃ ግብር በአጫጭር ስልጠናዎች፣ በዲፕሎማና በዲግሪ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ስልጠና ሲከታተሉ የቆዩ 1 ሺህ ባለሙያዎችን ያስመርቃል።
ዓለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በዘርፉ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን በትንሹ 60 በመቶ ብቃት ያለው ሙያተኛ ያስፈልጋል።