የኢትዮ-ኩባ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-ኩባ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ ግንቦት 21/2011 የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የኩባውን ምክትል ፕሬዚዳንት ሳልቫዶር አንቶኒዮ ቫልዴዝን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።
ውይይቱን የተከታተሉት በፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት የፕሮቶኮልና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረች ወቅት ኩባውያን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የከፈሉትን መስዋዕትነት የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ምንግዜም የሚያስታውሱት ተግባር እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ከኩባ ጋር ያላትን በሰማዕትነት የተሳሰረ ግንኙነት አጠናክራ ለማስቀጠል ጽኑ ፍላጎት ያላት መሆኑንም ፕሬዚዳንቷ ተናግረዋል።
ኩባ ከስድስት ሺህ በላይ ለሚልቁ ኢትዮጵያውያን የትምህርት እድል በመስጠት ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ያደነቁት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ አገራቸው በቀጣይም ኩባ ያላትን ሰፊ የተማረ የሰው ሃይል ለመጠቀም እንደምትፈልግ ጠቁመዋል።
በርካታ ኩባውያን በኢትዮጵያ በግብርና፣ በህክምናና በከፍተኛ የትምህርት ዘርፍ እያከናወኑ ያሉትን ተግባራትንም አድንቀዋል።
የኩባ ምክትል ፕሬዚዳንት ሳልቫዶር አንቶኒዮ ቫልዴዝ በበኩላቸው የኢትዮጵያንና የኩባን ግንኙነት አጠናክሮ ለማስቀጠል አገራቸው ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።
በአቅም ግንባታው ዘርፍ የተጀመረው ግንኙነትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል መግባታቸውን ውይይቱን የተከታተሉት አቶ አሸብር ገልጸዋል።
የኩባ ምክትል ፕሬዚዳንት ሰልቫዶር አንቶኒዮ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ይገኛል።
የኩባው ምክትል ፕሬዚዳንት ዛሬ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር ደመቀ መኮንን ጋር የተወያዩ ሲሆን፤ ውይይቱ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው።
ሁለቱ አገሮች በጤና፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በትምህርት የሚያደርጉትን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችሉ ሀሳቦች በውይይታቸው አንስተዋል።
እንዲሁም በስኳር ማምረትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ትብብር ለማድረግም ተሰማምተዋል።
ከምክትል ፕሬዚዳንቱ ጋር የአገሪቷ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አና ጎንዛሌዝ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ አማካሪ ብርጋዴር ጀኔራል ኤርናልዶ ታማዮ ጉብኝት በማድረግ ላይ ናቸው።
በቆይታቸው ከሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።