የሠላም ሚዲያ ኔትዎርክ ትስስር ስምምነት ተፈረመ - ኢዜአ አማርኛ
የሠላም ሚዲያ ኔትዎርክ ትስስር ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ ግንቦት 21/2011 የሠላም ሚዲያ ኔትዎርክ ትስስር ስምምነቱን የተፈራረሙት የሠላም ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ብሮድካስተሮች ዘርፍ ማህበር ናቸው፡፡
ስምምነቱ በኢትዮጵያ ግጭት፣ ሁከትና ብጥብጥ እንዳይፈጠር በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማትና ግለሰቦች ሠላምን የጋራ አጀንዳቸው ማድረግ የሚያስችላቸው ነው ተብሏል።
ከኢትዮጵያ ብሮድካስተሮች ማህበር ሊቀ መንበር አቶ አማን ፍስሃጽዮን ጋር ስምምነቱን የፈረሙት የሠላም ሚኒስትር ዴኤታዋ አልማዝ መኮንን በኢትዮጵያ አሁን ያለውን የሠላም መደፍረስ ለመከላከል በጋራ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
''ሠላም በጥቂት ተቋማት ወይም ግለሰቦች ጥረት ብቻ የሚመጣ ባለመሆኑ ሁሉም አካላት በሠላም ግንባታ ላይ በንቃት መሳተፍ አለባቸው'' ብለዋል።
ከማህበሩ ጋር የተደረሰው ስምምነትም በአገሪቱ ዘላቂ ሠላም ለማምጣት መገናኛ ብዙሃን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ተፅዕኖ እየጎላ መምጣቱን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ ይህን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ተጠቅመው ለዘላቂ ሠላምና ዕድገት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
መገናኛ ብዙሃን የሠላም ጋዜጠኝነትን በመጠቀም ሙያዊ ሥነምግባራቸውን አክብረው እንዲሰሩ የጠየቁት ወይዘሮ አልማዝ በስራቸው ላይ መንግስት ጣልቃ እንደማይገባ አረጋግጠዋል።
መንግስት የሙያ ሥነ ምግባራቸውን ጠብቀው ለሠላም የሚሰሩ መገናኛ ብዙሃንን ከማገዝ ውጪ ምንም ዓይነት አሉታዊ ተፅዕኖ እንደማያሳድር በመጥቀስ።
በዜጎች መካከል መጠራጠርን ለማስወገድና ለዘመናት የዘለቀውን የአብሮነት እሴት ለማጎልበት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስተሮች ማህበር ሊቀ መንበርና የኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን መስራች አቶ አማን ፍስሃጽዮን እንዳሉትም መገናኛ ብዙሃን ለሠላም ጋዜጠኝነት የሙያ ሥነ ምግባርን ማክበር አለባቸው።
ስምምነቱን የፈረሙት የቢዝነስ መገናኛ ብዙሃን ተቋማት መሆናቸውን ገልጸው የስምምነት መመሪያውን የሚቀበል ማንኛውም የመገናኛ ብዙሃን ተቋም ወይም ግለሰብ መሳተፍ እንደሚችል ተናግረዋል።
መገናኛ ብዙሃን የራሳቸው ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ቢኖራቸውም የሁሉም መሰረት ለሆነው ሠላም ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።
''ግጭቶች በተከሰቱበት አካባቢ የጉዳቱን መጠን፣ ዓይነትና ጥልቀት በምርመራ ዘገባ በማረጋገጥ ትክክለኛ መረጃ ለኅብረተሰቡ ማድረስ ይጠበቅብናል'' ነው ያሉት።
አክለውም መረጃ በሚፈልጉ ጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ወከባ፣ እንግልትና ጥቃት መቆም እንዳለበት ተናግረዋል።
አልፎ አልፎ በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት መንግስት መከላከልና ለደህንነታቸውም ዋስትና መስጠት እንደሚገባውም አመልክተዋል።