ቀጥታ፡

ለጠንካራ ሃገራዊ አንድነት የጋዜጠኞችና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ሚና ጉልህ ነው… የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር

ደብረ ብርሃን ግንቦት 21/2011 የወጣቱ ትውልድ በፍቅርና በአንድነት የታነፀ ጠንካራ አገራዊ አስተሳሰብ እንዲጎለብት ጋዜጠኞችና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አሳሰበ።
በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ "ባህልና ኪነጥበብ ለማህበረሰብ ሰላም ፍቅርና አንድነት” በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ የነበረዉ 6ኛው የባህል አውደ ጥናት ተጠናቋል።

የማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ አበረ አዳሙ ለኢዜአ እንዳሉት ወጣቱ የሀገሩን ባህል፣ ወግና ልማድ ጠብቆ እንዲኖር የኪነጥበባት ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች ስለ ሰላም ፍቅር አበክረው ሊያስተምሩ ይገባል።

በተለይም አሁን ሃገሪቱ ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት እርስ በእርስ መተሳሰብ እንዲሰፍን ጥበብ በተሞላበት መንገድ መስራት ይገባል።

የሀገርን ሰላም ለማስፈን ማህበሩ በየወሩ "ብሌን” ኪነጥበባዊ የሰላም ምሽት በሚል በአዲስ አባባ በማዘጋጀት በእውቀት ላይ የተመሰረተ መልእክት ለወጣቱ በማስተላለፍ ላይ ነው።

“ፖለቲከኞች ወደ ነፍሳቸው ተመልሰው ድንጋይ ከመወርወርና ጥይት ከመተኮስ እስኪመለሱ ድረስ ገለልተኛ ተቋማት ለሀገር ሰላም መስራት አለብን” ብለዋል።

“የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጀመረው የባህል ጥናትና ምርምር ማህበረሰቡን ያማከሉ እንዲሆኑና የተደበቁ ባህሎች ወጥተው ለሀገር ግንባታ ጥቅም እንዲውሉ ማህበሩ ያግዛል” ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እጩ ዶክተር ውዳላት ገዳሙ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲዉ በተከታታይ አመታት በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ዘርፍ የሚያካሂደው ጥናትና ምርምር የዜጎችን ስነ-ምግባር ለመቅረጽ የሚያግዝ ነው።

ሰሜን ሸዋ በታሪክ፣ በባህልና ኪነጥበብ በቅርስ ጥናት ሰፊ የሚሰሩ ስራዎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ “በሀገር በቀል ስራዎች ላይ የወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የአካባቢን ሰላም ማስጠበቅ ይገባል”ብለዋ።

ማንነቱንና የአባቶቹን ዳራ ያወቀ ወጣት በማፍራትም አሁን ላይ በሀገሪቱ የሚስትዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ባህልንና ኪነ-ጥበብን ለወጣቱ ማሳወቅ ተገቢ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ የጥናትና ምርምር ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አልማዝ አፈራ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲያቸው የአካባቢን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

“የአማራ ክልል ህዝብ መንፈሳዊ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቁርኝቱ ከሌሎች ህዝቦች ጋር ያለውን አንድነት በማሳየት ለሀገር ግንባታ እየተሰራ ነው”ብለዋል፡፡

በቀጣይ ሰኔ ወርም ሸዋን ለማስተዋወቅ በደብረብርሃን ከተማ የሸዋ ፌሰቲቫል ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡

በአውደ ጥናቱ ዩኒቨርሲቲዎችና የአብነት ትምህርት ቤቶች ትስስር በኢትዮጵያ ፣ የአማርኛ ቋንቋ ዘዬዎች የድምጸ-ልሳን ልዩነት የግዕዝ ቋንቋና መሰል 22 ጥናታዊ ጽፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ከግንቦት 19 እስከ 20/2011 በተካሄደው አውደ ጥናት ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም