ቀጥታ፡

ተቋማት ለግል ባለሃብቱ መተላለፋቸው በልማታዊ መንግስትነቱ ላይ ለውጥ አያመጣም ... ምሁራን

አዲስ አበባ ግንቦት 30/2010 ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ  ሰሞኑን ሜጋ ፕሮጀክቶቹ ድርሻ ላይ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች ሀገሪቷ በምትከተለው የልማታዊ መንግስት ርዕዮት ላይ የሚያመጣው መሰረታዊ ለውጥ እንደሌለ የምጣኔ ኃብት ምሁራን ገለጹ። የኢህአዴግ  ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከትናንት በስቲያ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው የባቡር፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክና የሆቴልን ጨምሮ በመንግስት ይዞታ ስር ያሉ የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ድርጅቶችን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክሲዮን ሽያጭ ወደ ግል ዘርፍ እንዲተላለፉ ወስኗል። የኢትዮ-ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች እና የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ትልቁን የአክስዮን ድርሻ መንግስት ይዞ ቀሪው አክሲዮን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ባለኃብቶች እንዲተላለፍም አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ የውሳኔው ዓላማ የምጣኔ ኃብት ዕድገቱን ፍጥነት ይበልጥ ለማስቀጠል፤ ብሎም እውቀትና የውጭ ምንዛሪ ያላቸው የውጭ ባለሃብቶች በዕድገቱ ላይ  አዎንታዊ ሚና እንዲያክሉ ማስቻል ነው ተብሏል። ኢዜአ ያነጋገራቸው የምጣኔ ኃብት ምሁራን እንደሚሉት ኮሚቴው ያስተላለፈው ይህ ውሳኔ "የዜጎችን ተጠቃሚነት ከማሳደግ ውጭ ወደሊብራል አስተሳሰብ አይመራም፤ ሀገሪቷ በምትከተለው የልማታዊ መንግስት ርእዮት ላይም የሚያመጣው መሰረታዊ ለውጥ የለም"። በሀገሪቷ "የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደግል የማስተላለፉ ተግባር ላለፉት 20 ዓመታት ሲከናወን የነበረ ነው" ያሉት ምሁራኑ፤ የአሁኑ ውሳኔ ከበፊቱ የሚለየው ኢትዮ-ቴሌኮምን ጨምሮ ግዙፍ ተቋማት ላይ ባለሃብቱ እንዲሳተፍ መንግስት መፍቀዱ መሆኑን ጠቅሰዋል። የፌር ፋክስ ሊቀመንበር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ በሰጡት አስተያየት በሀገሪቷ ምጣኔ ኃብታዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የግል ዘርፉ መዋእለ ንዋዩን በማፍሰስ እንዲሳተፈ መፍቀዱ "የመንግስትን ልማታዊነት አይለውጠውም" ብለዋል። ይህን መሰሉን ውሳኔ እንደ ቻይና፣ ኮሪያና ሲንጋፖር የመሳሰሉ የልማታዊ መንግስት ባህሪ ያላቸው ሀገራት ጭምር ተግባራዊ አደርገውታል፤ ሆኖም ግን ልማታዊ መንግስትነታቸው ላይ ያመጣው ለውጥ አለማምጣቱም ለአብነት ጠቅሰው ያብራራሉ።  በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሲዬሽን የዘርፉ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር አሰፋ አድማሴ በበኩላቸው በተላለፈው ውሳኔ  መሰረት የግሉ ዘርፍ በምጣኔ ኃብታዊ እንቅስቃሴው ቢሳተፍም የመሪነት ሚናውን የሚጫወተው መንግስት በመሆኑ "ርዕዮት የሚያስቀይር ምንም ነገር የለም" ይላሉ። የመንግስት እርምጃ የህዝቡን ማህበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ተጠቃሚነት ለማሻሻል በማሰብ ነውም ብለዋል። በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት መምህር አቶ መዚድ ናስር እንደሚሉት ደግሞ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ገበያ መር ምጣኔ ኃብታዊ አስተሳሰብን ሙሉ በሙሉ መከተል አስተማማኝ አይደለም። በመሆኑም "ልማታዊነቱን ያልለቀቀ ሆኖ ግን ባለኃብቱን አሳታፊ የሚያደርግ ስርዓት መኖሩ መልካም ነው"  ሲሉም ተናግረዋል። እንደ አቶ መዚድ አስተያየት እ.አ.አ. በ2008 በአሜሪካና በአውሮፓ ሀገራት የታየው የምጣኔ ኃብት ቀውስ የመንግስት ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ መሆኑን ያረጋገጠ ክስተት ነው።  "ምጣኔ ኃብታዊ ሂደቱን ባልተቀናጀ የገበያ ስርዓትና ስነ-ምግባር በሌለው ገበያ እንዲመራ ማድረግ የበለጠ ውድቀት ሊያመጣ ስለሚችል መንግስት ቁጥጥር በማድረግ በትብብር ለመስራት መወሰኑ በበጎ የሚታይ ነው" ሲሉም አቶ መዚድ ይናገራሉ። ሆኖም ውሳኔው መተግበር ያለበት በጥናትና በጥንቃቄ የተዘጋጀ መመሪያን በመከተል መሆን እንዳለበትም ምሁራኑ ይመክራሉ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም