ቀጥታ፡

ሰብአዊ መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ ይገባል... የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን

ደብረ ማርቆስ ግንቦት30/2010 የህግ የበላይነትን በማክበርና በማስከበር ሰብአዊ መብቶች እንዳይሸራረፉ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ገለጸ። የአማራ ክልል ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በዜጎች ሰብአዊ መብት አከባበር ላይ ለጸጥታ አካላት በደብረ ማርቆስ ከተማ ስልጠና ሰጥቷል። የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ እሸት ገብሬ በእዚህ ወቅት እንደገለፁት ሰው በመሆን ብቻ የተሰጠ ሰብአዊ መብት እንዳይጣስ የሁሉም አካላት ቅንጅታዊ ጥረት ያስፈልጋል። "በተለይ የፀጥታ አካላትና ማረሚያ ቤቶች በግንዛቤ እጥረትም ሆነ በድፍረት የመብት ጥሰት እንዳይፈጽሙ ተባብሮ ከመስራት ባለፈ የህግ የበላይነትን ማክበርና ማስከበር ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል። የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ብናልፍ አንዷለም በበኩላቸው የዜጎች ሰብአዊ መብት አያያዝና አጠባበቅን በተመለከተ  በተጠያቂነት መንፈስ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል። "በህገ መንግስቱ የተቀመጡ የዜጎች ሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ላይ ክፍተት አለ" ያሉት አቶ ብናልፍ፣ የሕብረተሰቡን ንቃተ ህሊና በማሳደግ ለመብቱ መከበር አጥብቆ የሚቆም ዜጋ ማፍራት እንደሚገባም አሳስበዋል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባህር ዳር ቅርንጫፍ ኮሚሽነር አቶ አበረ ሙጨ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት የሰብአዊ መብቶች አያያዝን ለማሻሻል ሲሰራ ቢቆይም አሁንም የሚስተዋሉ የተወሰኑ ክፈተቶች አሉ። በህግ ጥላ ስር ያሉ ተጠርጣሪዎችን በ24 ሰዓት ውስጥ ለፍርድ ቤት አለማቅረብ፣ የተጠርጣሪውን መብትና ግዴታ አለማሳወቅ፣ የሰጠውን ቃል በትክክል አንብቦ አለማስፈረምና መሰል የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለአብነት ጠቅሰዋል። ስልጠናው በፀጥታ አካላት የሚስተዋለውን የግንዛቤ እጥረት ችግር በመፍታት የሰብአዊ መብቶች እንዳይጣሱ ለማድረግ ያለመ ነው። ስልጠናው ሰብአዊ መብትን ለማስከበር የፖሊስና የማረሚያ ቤቶች ድርሻ፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችና መሰል ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን 80 የሚሊሻ፣ የፖሊስና የማረሚያ ቤት አመራሮችም ተሳታፊ ሆነዋል። በስልጠናው ላይ የተሳተፉት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የሰው ሀብት ልማት ዋና የሥራ ሂደት ኦፊሰር ኢንስፔክተር ዘመን ዮሐንስ ስልጠናው የነበረባቸውን የእውቀት ክፍተት የሚሞላ ነው። በቀጣይም የዜጎችን ሰብአዊ መብት በአግባቡ በመጠበቅ በኩል ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ የሚያግዝ መሆኑን አመልክተዋል። በስልጠናው ያገኙትን እውቀት በኮሚሽኑ ላሉ አባላት እንዲሁም የህብረተሰቡን ንቃተ ሕሊና በማሳደግ የዜጎች መብት ሳይሸራረፍ እንዲጠበቅ የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ከማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን አገልግሎትና ቅሬታ ማስተናገጃ ዳሬክቶሬት የመጡት ኮማንደር አለሙ መንገሻ በስልጠናው በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ሁሉም ማረሚያ ቤቶች እንዲፈተሹና ያሉትን ችግሮች ለመለየት የሚያስችል ግባቶች ማግኘታቸውን ተናግረዋል። በደብረ ማርቆስ ከተማ ከግንቦት 25 እስከ 29 ቀን 2010 ዓ.ም ሲሰጥ የቆየው የአሰልጣኞች ስልጠና ትናንት ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም