ቀጥታ፡

በትረስት ፈንዱ ከዳያስፖራው የተሰበሰበው 4 ሚሊዮን ዶላር ለልማት ሊውል ነው

አዲስ አበባ ግንቦት 21/2011 የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የሰበሰበውን 4 ሚሊዮን ዶላር ለዘላቂ የልማት ፕሮጀክቶች ሊያውል መሆኑን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ በውጭ አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሰባሰበውን 4 ሚሊዮን ዶላር ለልማት ፕሮጀክቶች ሊያውል መሆኑን አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለዳያስፖራ ማህበረሰብ የትረስት ፈንድ እንዲቋቋም ባቀረቡት ጥሪ መሰረት ጥቅምት 13 ቀን 2011 ዓ -ም ትረስት ፈንዱ በይፋ ገንዘብ ማሰባሰብ መጀመሩ ይታወሳል።

በቅርቡ በኢትዮጵያ  ቦርድና ጽህፈት ቤት በማቋቋም የተለያዩ ስራዎችን ማከናወን ጀምሯል።

እስካሁንም በተለያዩ አገሮች ከሚኖሩ 20 ሺህ ኢትዮያውያን የተሰበሰበውን 4 ሚሊዮን ዶላር ለዘለቂ ልማት ለማዋል ከሚመለከታቸው ባለደርሻ አካላት ጋር ምክክር እያደረገ ነው።

የልማት ፕሮጀክቱ በዋነኝነት በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በውሃ፣ በሴቶች ጉዳይና አካል ጉዳተኞች ላይ በትኩረት ይሰራል ተብሏል።

ፕሮጀክቶቹ የህብረተሰቡን መሰረታዊ ችግሮች በአጭር ጊዜ መፍታት የሚችሉ መልካም አጋጣሚዎችን የሚፈጥሩ እንደሚሆኑም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ  ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቅሬ ዘውዴ እንዳሉት ትረስት ፈንዱ ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከትና ተጽዕኖ ነጻ ሆኖ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በእኩል ለመደገፍ የተቋቋመ ነው።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮያውያን ለረጅም ዓመታት በአገራቸው ልማት ላይ ለመሳተፍ በርካታ ተግዳሮቶች እንደነበረባቸው አስታውሰው ከመጣው ለውጥ ጋር ተያይዞ በርካታ ዳያስፖራዎች ልማቱን ለመደገፍ ፍላጎት አሳይተዋል።

ከዳያስፖራው የሚሰበስበው ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ ለዘላቂ ልማት የሚውል ሲሆን ለጽህፈት ቤቱና ለሌሎች ወጪዎች ደግሞ ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም በተገኘ ድጋፍ የሚከናወን መሆኑንም አስረድተዋል።

መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሲቪክ ማህበራትና እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍል በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ማድረግ አንደሚችሉም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ አማካሪ አባላት አምስት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ሦስት ከሴቶች፣ ከወጣቶችና ከነዋሪዎች የተውጣጡ አባላት ያሉት የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮችና ሦስት የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካዮች ይገኙበታል።

የፈንዱ የዳይሬክተሮች ቦርድ የፈንዱን አጠቃላይ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂ፣ ቁጥጥርና ተጠያቂነት የሚያስተዳድር የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የበላይ ነው።

ከሥራዎቹም መካከል በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ተለይተው የሚታወቁና የተረጋገጡ ፕሮጀክቶችን ድጋፍ በመመርመር የሚያጸድቅ ነው።

የትረስት ፈንዱ አማካሪ ዶክተር ብስራት አክሊሉ በበኩላቸው በተለያዩ የዓለም አገሮች ኢትዮያውያን ያሉ ቢሆንም እስካሁን ለአገራቸው ዘላቂ ልማት የሚፈለገውን አስተዋጽኦ ሲያደርጉ እንዳልነበር ነው የተናገሩት።

እስካሁን የተሰበሰበው ዶላር ዳያስፖራው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመት በኋላ በአገሪቷ የመጣውን ለውጥ በመደገፍ ያዋጣው መሆኑንና በቀጣይም ገቢው ወደ ተግባር ገብቶ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ሲያደርገ ለሌሎችም ተነሳሽነትን ይፈጥራል ብለዋል።

ህብረተሰቡ ፈንዱ ሁሉንም የአገሪቷ ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚያደርግና ለዚህ ደግሞ የሁሉም ዜጎች ተሳትፎና ሃላፊነት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

የህብረተሰቡን ችግሮች መንግስታዊ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በሚያቀርቡት ፕሮፖሳል መሰረት ተፈትሾ ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ነው ያመለከቱት።

ፕሮጀክቶቹ በቦርዱ ተፈትሸው ከተመረጡ በኋላ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ይፋ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም