ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ መሬት ለተገቢው ጥቅም እንዲውል የሚያግዝ ፖሊሲ ባለመኖሩ ብክነት አስከትሏል

ግንቦት 20/2011 በኢትዮጵያ መሬት ለተገቢው ጥቅም እንዲውል የሚያግዝ ፖሊሲ ባለመኖሩ በሀብቱ ላይ ጉዳት ደርሷል ሲል ብሔራዊ የተቀናጀ መሬት አጠቃቀም ዕቅድ ዝግጅትና ፖሊሲ ፕሮጀክት ገለጸ።

መሬት ለተገቢው ጥቅም እንዲውል በሚያስገድድ ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ባለድርሻ አካላት በባህር ዳር ከተማ ውይይት አድርገዋል፡፡

የፕሮጀክቱ የህግ ባለሙያ  አቶ ቡልቻ በሬቻ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት እንደ ሀገር ወጥ የሆነ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ አልነበረም።

ይህ ባለመሆኑ የአገሪቱን መሬት ለተገቢው አገልግሎት እንዲውል በማድረግ በኩል  ችግር ሲፈጠር መቆየቱን አስታውሰዋል።

በዚህም  ለም የእርሻ መሬቶችን ለከተማ ህንጻዎችና  ለኢንዱስትሪ ግንባታ ማካሄጃዎች  እንዲውሉ እንዲሁም  ለእርሻ አገልግሎት የማይውል መሬት ደግሞ ለእርሻ አግልግሎት እንዲውል የተደረገበት ሁኔታ መኖሩን ገልፀዋል፡፡

“በተጨማሪም የደን ቦታዎችና ጥብቅ ስፍራዎች ለከተማ መስፋፋትና ለሌሎች ግልጋሎቶች እንዲውሉ ተደርጓል”  ብለዋል አቶ ቡልቻ።

ይህ  የሆነው መሬትን ለተገቢው አግልግሎት ለይቶ የሚያውል የመሬት አጠቃቀም  ፖሊሲ አገሪቱ ሊኖራት ባለመቻሉ መሆኑንም ገልጸዋል።

እንደአቶ ቡልቻ ገለጻ መሬትን ለተለያየ ጉዳይ የሚጠይቁ 16 ተቋማት በየራሳቸው መመሪያ  መሬትን እንደፈለጋቸው እየተጠቀሙበት ይገኛል።

ሃገሪቱ ፖሊሲ የሌላት በመሆኑ የገጠሟትን ችግሮች ሊፈታ የሚያስችልና ባለድርሻ አካላትን ያካተተ  የተቀናጀ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲተዘጋጅቶ ውይይት እየተደረገበት መሆኑንም ተናግረዋል።

ፖሊሲው የባለድርሻ አካላት አስተያየት ከታከለበት በኋላ  በሚቀጥለው ዓመት ሥራ ላይ ለማዋል ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አቶ ቡልቻ አመልክተዋል፡፡

የአማራ ክልል የገጠር መሬት  አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ የገጠር መሬት  አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ  ታምራት ደምሴ በበኩላቸው”  የተቀናጀ የመሬት አስተዳደር ፖሊሲ ባለመኖሩ መሬቶች ላልተገባ የልማት ዝርፍ እየዋሉ ነው” ብለዋል።

በተለይም የእርሻ መሬቶችን ለኢንዱስትሪ ፓርክና  ለከተሞች ማስፋፊያ  አገልግሎት  እየዋሉ በመሆናቸው በምርት ላይ ከፍተት እየተፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል።

የመሰረተ ልማት አውታሮች ዝርጋታ  በመግባባት ላይ የሚከናወኑ ባለመሆናቸውና አንዱ ሲያለማ ሌላው እያፈረሰ  ለመሬት መሸርሸርና  ለኢኮኖሚ ድቀት እየዳረገ መሆኑን ገልፀዋል።

 “እንደ አማራ ክልል የተቀናጀና ባለድርሻ አካላትን ያግባባ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲሆን አስፋላጊውን ትብብር እናደርጋለን” ብለዋል።

“መሬት አንጡራ ሃብቷ  ለሆነ አገር እስካሁን የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ አለመኖሩ የዘርፉን ምሁራንም ሆነ ተቋማትን የሚያስወቅስ ነው” ያሉት ደግሞ የትግራይ ክልል የአካባቢ ጥበቃና መሬት አጠቃቀም ኤጀንሲ  የመሬት አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ አረቡ ይማም ናቸው።

ወጥ የሆነ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ባለመኖሩ እንደትግራይ ክልልም ሆነ እንደ ሃገር ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሰ ስለሆነ ፖሊሲው በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገባ  ተገቢውን እገዛ እንደሚያደርጉ አመልክተዋል።

በባህር ዳር ከተማ ለሁለት ቀናት በተካሄደው የምክክር መድረክም ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸው ታውቋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም