ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በፊፋ የአገሮች እግር ኳስ ደረጃ አምስት ደረጃዎችን ቀነሰች

አዲስ አበባ ግንቦት 30/2010 ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (ፊፋ) ዛሬ ይፋ ባደረገው የሰኔ ወር የሀገሮች ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ ኢትዮጵያ በአምስት ደረጃዎች ዝቅ ብላለች። በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ በግንቦት ወር ከነበረችበት 146ኛ ደረጃ ወደ 151ኛ ወርዳለች። በታህሳስ ወር 2010 ዓ.ም በኬንያ አስተናጋጅነት ከተካሄደው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ሀገሮች የዋንጫ ውድድር በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምንም አይነት ጨዋታዎችን አድርጎ አያውቅም። የቀድሞው የቡድኑ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ታህሳስ ወር ላይ ሥራቸውን ከለቀቁ በኋላም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እስካሁን አዲስ አሰልጣኝ አልሾመም። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እ.አ.አ 2019 በካሜሮን ለሚካሄደው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ለማለፍ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን በመጪው ነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም ከሴራሊዮን አቻው ጋር ያደርጋል። ፊፋ ዛሬ ይፋ ባደረገው የሀገሮች እግር ኳስ ደረጃ መሰረትም ጀርመን፣ ብራዚል፣ ቤልጂየም፣ ፖርቹጋልና አርጀንቲና ከአንድ እስከ አምስት ያለውን ደረጃ የያዙ ሲሆን ስዊዘርላንድ፣ ፈረንሳይ፣ ፖላንድ፣ ቺሊና ስፔን ከስድስት እስከ አስር ባለው ደረጃ ተቀምጠዋል። ቱኒዚያ 21ኛ፣ ሴኔጋል 27ኛ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 38ኛ፣ ሞሮኮ 41ኛ እና ግብጽ 47ኛ ደረጃ በመያዝ ከአፍሪካ የተሻሉ ሀገራት ለመሆን ችለዋል። አዘርባጃን 21 ደረጃዎችን አሻሽላ ወደ 105ኛ በመምጣት በወሩ ከፍተኛ የደረጃ ማሻሻል ያሳየች ሀገር ሆናለች። በአንጻሩ የደቡብ አሜሪካዋ ጉያና 18 ደረጃዎችን አሽቆልቁላ ወደ 182ኛ ደረጃ ወርዳለች። ተርክስና ካይኮስ ደሴቶች፣ አንጉሊያ፣ ባህማስ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያና ቶንጋ የመጨረሻውን 206ኛ ደረጃ ይዘዋል። በሴቶች የፊፋ የሀገሮች የእግር ኳስ ደረጃ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሉሲዎቹ 118ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን ቀጣይ ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ ሰኔ 15 ቀን 2010 ዓ.ም የሚወጣ ይሆናል። የፊፋ ወርሐዊ የአገሮች ደረጃ የሚወጣው ፊፋ እውቅና በሰጣቸው ውድድሮች ላይ ብሔራዊ ቡድኖች ባስመዘገቡት ውጤት በሚሰጣቸው ነጥብ አማካኝነት ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም