ሜጋ ፕሮጀክቶችና ኩባንያዎች ለግል ባለሃብቶች እንዲዛወሩ መወሰኑ የምርት ጥራትን ይጨምራል -የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች - ኢዜአ አማርኛ
ሜጋ ፕሮጀክቶችና ኩባንያዎች ለግል ባለሃብቶች እንዲዛወሩ መወሰኑ የምርት ጥራትን ይጨምራል -የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች
አዲስ አበባ ግንቦት 30/2010 ሜጋ ፕሮጀክቶችና ትልልቅ የመንግስት ኩባንያዎች ለግል ባለሃብቶች እንዲዛወሩ መወሰኑ የተቋማቱን የምርት ጥራት በመጨመር የኢኮኖሚ እድገቱን እንደሚያፋጥን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ገለፁ። የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የኢትዮ-ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች እና የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ትልቁን የአክስዮን ድርሻ መንግስት ይዞ ቀሪው አክሲዮን ለአገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሃብቶች እንዲተላለፉ ወስኗል። በመንግስት ይዞታ ሥር ያሉና በማምረት ወይም አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም በግንባታ ላይ የሚገኙ የባቡር፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የሆቴል እና የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክሲዮን ሽያጭ ወደ ግል ዘርፍ እንደሚተላለፉ በውሳኔው ተካቷል። ውሳኔውን አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሃበት ባሙያዎች ከ20 አመት በፊት ጀምሮ ሆቴሎች የቢራ ፋብሪካዎች ለግል ባለሀብቶች ሲዛወሩ ቆይተዋል፤ ይህን ውሳኔ ለየት የሚያደርገው የግል ባለሀብቶችን በትልልቅ ፕሮጀክቶች በማሳተፍ የንግድ ውድድርን በመፍጠር ጥራትን ለመጨመር ማስቻሉ ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ማህበር ዋና ተመራማሪ ዶክተር አሰፋ አድማሴ እና የፋየር ፋክስ ፈንድ ሊቀመንበርና የኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ መንግስት የግል ባለሀብቱን አቅጣጫ በማመልከት የግል ባለሀብቱ ሊገባበት ያልቻለውን ክፍተት እያየ የመሙላት፣የልማት አቅጣጫው ምን መምሰል አለበት የሚለውን የመወሰን ስራ መስራት አለበት ይላሉ። በመንግስት ተይዘው ውጤታማ ያልሆኑ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ጠቁመው ለግል ባለሀብቱ ከተላለፉ የግል ባለሀብቶች መንግስትን በማገዝ ተጨማሪ ሀብት በማምጣት ኢኮኖሚውን ያሳድጋሉ ብለዋል። ብቃት ያለው የሰው ሀይል በመያዝ ፣ የተሻለ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸው ባለሃብቶች ከተሰማሩባቸው ድርጅቶቹን አለም አቀፍ ተወዳደሪ ማድረግ ያስችላቸዋል ብለዋል። እንደ ባለሞያዎቹ ገለጻ ድርጅቶቹ ለግል ባለሀብቶች ቢተላለፉ የንግድ ውድድርን በመፍጠር ጥራት ያለው ምርት በፍጥነት ተደራሽ በማድረግ ዜጎች የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋልም ብለዋል ። በዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር ፋሲል ጣሰው በበኩላቸው እነዚህ ብሄራዊ ግዙፍ ኩባንያዎች የግል ባለሃብቶች ሲገቡባቸው የተቋማቱን ተወዳዳሪነትና ጥራት ያለው አገልግሎት አሰጣጥ አቅምን ያሳድገዋል ብለዋል። በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር መዚድ ናስር በበኩላቸው ውሳኔውን ተከትሎ በአጭር ጊዜ የግል ባለሀብቱ ገንዘብ ለሀገር ልማት እንዲያውል ያስችላል ብለዋል። የምርት ጥራትን እና ተወዳዳሪነትን ለመፍጠር ግን በአንድ ዘርፍ ላይ በርካታ ባለሀብቶች እንዲሰማሩና ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ ሌሎች ድርጅቶችን መፈጠር እንዳለባቸው የቴሌኮም አገልግሎትን ለአብነት በማንሳት ያስረዳሉ። ውጤታማና አለም አቀፍ እውቅናን ያገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጉዳይ ግን መንግስት በጥንቃቄ መመልከት እንዳለበት ሁሉም በአንድ ድምፅ አሳስበዋል። መንግስት ድርጅቶቹን መሸከም የሚችል የኢኮኖሚ እና አስተዳደር ያለው ባለሀብት መኖሩን የማረጋገጥ ሀላፊነት እንዳለበትም አሳስበዋል። ውሳኔው የትኛው መስክ ለባለሃብቶች እንዴት መተላለፍ አለበት የሚለውን በጥንቃቄ የሚያሳይ፤ችግሮች እንዳይፈጠሩ የሚረዳና ቢፈጠሩ እንኳን ሊፈታ የሚችልና ችግሮች እንዳይከሰቱ በሚከላከል የፖሊሲና ህግ ማዕቀፍ መታገዝ አለበት ብለዋል።