ቀጥታ፡

በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ተከስቶ ለነበረው የጸጥታ ችግር የተጠረጠሩ ተማሪዎች ተያዙ

ግንቦት 20/2011በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች መካከል በቅርቡ ተከስቶ የነበረውን ግጭት አነሳስተዋል  ተብሎ የተጠረጠሩ ሰባት ተማሪዎች መያዛቸውን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስታወቁ።

ተማሪዎቹ ትርምስ የመፍጠር ተልዕኮ ባላቸው ኃይሎች የተነሳሱ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ በተቋሙ ተከስቶ የነበረውን የጸጥታ ችግር አስመልክቶ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር እየተወያየ ነው።

የዩኒቨርሰቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ እንዳሉት ችግር ፈጣሪዎቹ ማንነታቸው እንዳይለይ በልብስና መሰል ነገሮች ተሸፋፍነው የተማሪ ሕብረት አባል የሆኑ ተማሪዎችን ለማጥቃት ባደረጉት ሙከራ የአንድ ሰው ሕይወት ሲጠፋ በሦስት ተማሪዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን አመልክተዋል።

በዚህም ዩኒቨርሲቲውም ሆነ የአካባቢው ማህበረሰብ ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸው የገለጹት ዶክተር ታፈረ  ለሟቹ ተማሪ ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶችና ጓደኞች መጽናናትን ተመኝተዋል።

በደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት እጃቸው ያለበት ወገኖችን ተቋሙ ሳይውል ሳያድር ከፀጥታ አካላትና ከማህበረሰቡ ጋር በመሆን ለህግ እንደሚያቀርባቸውም ቃል ገብተዋል።

“ድርጊቱ የተፈጠረው ሆን ተብሎ የአካባቢውን ማህበረሰብ ስነልቦና ለመስበርና አማራ ህዝብ መገለጫ የሆነውን ፍቅርና አብሮነት ለማጠልሸት ነው” ያሉት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሀም አለኸኝ ናቸው።

የአማራ ብሎም የደብረማርቆስ ህዝብ ተግባር ያልሆነውን ጨካኝነት በተልዕኮ እየፈፀሙ ያሉ አካላት አደብ እንዲይዙና አጥፊዎችም ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ አስፈላጊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስረድተዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል በደብረማርቆስ ከተማ የቀበሌ 04 ነዋሪ አቶ አሰፋ አልማው በተከሰተው ችግር እጅግ ማዘናቸውንና ድርጊቱ የደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪዎችን  እንደማይወክል ተናግረዋል።

"ዩኒቨርሲቲ ያሉ ተማሪዎች ባንወልዳቸውም ልጆቻችን ናቸው፣ ነገር ግን አንዱን ከሌላው ለመለያየትና ለመነጣጠል ሲባል የራሳቸው አጀንዳ እንዲፈፀምላቸው እያደረጉ ባሉ  አካላት ላይ መንግስት ጥብቅ እርምጃ ሊወስድ ይገባል"።

ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር በመሆን አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹትአቶ አሰፋ ፣  ችግሩን የፈጠሩና እንዲፈጠር ምክንያት የሆኑ ግለሰቦችን የፀጥታ አካላት ተከታትለው ለፍትህ እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።

አቶ ሙሉአለም አጥናፉ በበኩላቸው “ዩኒቨርሲቲዎች የዕውቀት እንጂ የተንኮል መጠንሰሻ መሆን የለባቸውም፤ የተከሰተው ችግር አሳዛኝ፣ አሳፋሪና የአማራን ህዝብ የማይወክል ነው” ብለዋል።

በቀጣይ እንደዚህ አይነት መሰል እኩይ ተግባር እንዳይከሰት ከዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ከፀጥታ አካላት ጋር ሆነው እንደሚሰሩም አስረድተዋል።

“የትኛውም እምነት ሰው ግደሉ አይልም፣ ይህ የነውረኞች ተግባር ነው” ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት አባት የሆኑት መጋቢ ሀላፍ ጥበቡ ሽታ  ናቸው።

“ በአደራ ልጆቻችን ላይ የደረሰው የሞትም ሆነ የአካል ጉዳት የእርስ በርስ ግንኙነታችን እንዳይጠናከር የሚፈልጉ ኃይሎች በመካከላችን እንዳሉ የሚያስገነዝብ ነው” ብለዋል።

በቀጣይ ተማሪዎች ስጋት እንዳይገባቸው ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ከጎናቸው እንዲሆን የጠየቁት መጋቤ ሀላፍ “ የዕምነት አባቶችም የክፋት ተልዕኮ ያላቸውን መምከርና መገሰፅ ይኖርብናል” ሲሉ ገልጸዋል።

ትናንት በነበረው የውይይት መድረክ ተወያዮቹ በማንኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚኖሩ የአማራ ማህበረሰብ እንዲሁም በአማራ ክልል የሚገኙ ማንኛውም የማህበረሰብ ክፍሎች የሚደርስባቸውን ጥቃት የሚያወግዝ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል።

በዩኒቨርሲቲው ተፈጥሮ በነበረው ችግር የአንድ ተማሪ ህይወት ሲያልፍ ሦስት  ተማሪዎች በደረሰባቸው ጉዳት ሕክምናቸውን እየተከታተሉ መሆናቸውን ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም