ቀጥታ፡

የትግራይ ክልል 13ኛው የኪነጥበብ ፌስቲቫል በኮረም ከተማ ተጀመረ

ግንቦት 20/2011 የትግራይ ክልል 13ኛው የኪነጥበብ ፌስቲቫል በኮረም ከተማ ተጀመረ።

ፌስቲቫሉን ያስጀመሩት የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብርክቲ ገብረመድህን ኪነጥበብ ታሪክ ለመስራትና የተሰራውን ለመጠበቅ የሚያስችል ኃይል እንዳለው ወጣቶች በመረዳት በእዚያ ልክ ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በኪነጥብ  ፌስቲቫሉ ላይ የተገኙት የትግራይ ደቡባዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ረዳኢ  አለፎም በበኩላቸው “ ኪነጥበብን ለፍቅር ፣ ለልማትና ለብልጽግና ማዋል ይገባል” ብለዋል።

"አካባቢያችን ለኪነጥበብ ፌስቲቫል ብቻ ሳይሆን ለልማትና ለኢንቨስትመንት  ምቹ ነው፤ ባለሀብቶች መጥተው ሊጠቀሙበት ይገባል” ያሉት ደግሞ የኮረም ከተማ ከንቲባ ዳርጌ መረሳ ናቸው፤

በፌስቲቫሉ ላይ ከ43 ወረዳዎች የተውጣጡ ከ1ሺህ 500 በላይ የኪነጥበብ ባለሙያዎችና አማተሮች  ተገኝተዋል።

ከግንቦት 20 እስከ ግንቦት 30 ቀን 2011 በሚቆየው በእዚህ የኪነጥበብ ፌስቲቫል ላይ  የቴአትር ፣ የሙዚቃ፣ የስነፅሁፍ፣ የስነ ስዕልና የቅርፃቅርፅ ሥራዎች ለእይታና ለውድድር እንደሚቀርቡ ታውቋል።

ባህልና ቋንቋቸውን በመግለፅ አርአያ ለሆኑ ወረዳዎችና ግለሰቦች የዕውቅና ምስክር ወረቀትና የገንዘብ ሽልማት እንደሚሰጥም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም