ለህዝቡ ጠንካራ አማራጭ ይዞ ለመቅረብ ውህደት ሊኖር ይገባል - ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለህዝቡ ጠንካራ አማራጭ ይዞ ለመቅረብ ውህደት ሊኖር ይገባል - ፓርቲዎች
ግንቦት 20/2011 በኢትዮጵያ በርካታ ቁጥር ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ለህዝቡ ጠንካራ አማራጭ ሆኖ ለመቅረብ መዋሃድ እንዳለባቸው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ገለጹ።
ፓርቲዎቹ ተመሳሳይ አጀንዳ ካላቸው ሌሎች ፓርቲዎች ጋር ለመዋሃድ ዝግጅት ላይ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
መንግስት ጠንካራ ፓርቲ እንዲፈጠር ተመሳሳይ አጀንዳ ያላቸውም ተዋህደው አብረው እንዲሰሩና አሁን ያለውን የፓርቲዎች ቁጥር እንዲቀንስ ፍላጎት እንዳለው ማሳወቁ ይታወሳል።
በሚቀጥለው አመት ይደረጋል ተብሎ ለሚታሰበው ምርጫ ህዝቡ ፓርቲዎቹን በአግባቡ እንዲያውቃቸው ቁጥራቸው መቀነሱ ያለው ሚና ቀላል የሚባል አይሆንም።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ግርማ በቀለ በኢትዮያ የፓርቲዎች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱን ገልጸው፤ ''ይህም የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋቱን የሚያሳይ ነው'' ብለዋል።
የፓርቲዎች አደረጃጀት በራሱ ችግር እንዳለበት ገልጸው ትክክለኛ የፖለቲካ ምህዳርን ለመፍጠር የፓርቲዎች ቁጥር ሊቀንስና ህዝቡም ስለ ፓርቲዎቹ ጠንቅቆ ማወቅ እንዳለበት ተናግረዋል።
የጋምቤላ ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ አስተባባሪ አቶ ታደለ ብሩ አንድነት ሃይል እንደመሆኑ በተበታተነ መልኩ ከመስራት በጋራ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራቱ ውጤታማ እንደሚያደርግ ያምናሉ።
ፓርቲያቸው ከሌሎች ስምንት ፓርቲዎች ጋር ግንባር መፍጠሩንና በቀጣይም ሌሎች መዋሃድ የሚፈልጉ ፓርቲዎችን በማካተት ጠንካራ አማራጭ የመሆን ሃሳብ እንዳለ ተናግረዋ።
የገዳ ስርዓት አራማጅ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሮበሬ ታደሰ ''ለህዝቡ ጠንካራ አማራጭ ለመሆን ሁለት ፓርቲ በቂ ነው'' ይላሉ።
በኦሮሚያ 14 የሚሆኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መኖራቸውን አስታውሰው እነዚህን ፓርቲዎች ወደ አንድ ለማምጣት የተለያዩ ስራዎችን እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮያ ብሄራዊ አንድነት ኮንግረስ ሊቀመንበር አቶ ገረሱ ገሳ ፓርቲዎች ከመዋሃዳቸው በፊት ግንባር በመፍጠር እርስ በእርስ በደንብ እንዲተዋወቁና ውህደቱን ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ፓርቲዎች በራሳቸው አደረጃጀትና በራሳቸው ውሳኔ የሚዋሃዱት በቦርዱ ህግና ደንብ መሰረት ነው።
ቦርዱ በአሁን ጊዜ የተለያዩ ህጎችን እያሻሻለ መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢዋ ከማሻሻያዎቹ መካከል የፓርቲዎች ምዝገባ እንደሚገኝበት ገልጸዋል።
ህጉ እስኪሻሻል ድረስ ቦርዱ ውህደት በመፍጠር አንደ አዲስ የሚመዘገቡ ፓርቲዎችን እያስተናገደ መሆኑን ገልጸው ይሁንና እስካሁን ለቦርዱ የቀረበለት የውህደት ጥያቄ ከሁለት እንደማይበልጥ አስታውቀዋል።