የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለተጠቀመው የተሳሳተ ካርታ ይቅርታ ጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለተጠቀመው የተሳሳተ ካርታ ይቅርታ ጠየቀ
አዲስ አበባ ግንቦት 20/2011 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድረ ገጹ ላይ ለተጠቀመው የተሳሳተ የአፍሪካ ካርታ በይፋ ይቅርታ ጠየቀ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው ጉዳዩን አስመልክቶ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግንቦት 17 ቀን 2011 ዓ.ም በተጠቀመው የተሳሳተ የአፍሪካ ካርታ ሶማሊያን አጠቃሎ የኢትዮጵያ አካል አድርጎ አሳይቷል።
''በተጨማሪም ሌሎች የአፍሪካ አገሮችን የፖለቲካ ድንበሮች የማያመላክት መሆኑን ተገንዝበናል'' ብለዋል።
የተሳሳተው ምስል በመስሪያ ቤቱ ድረ ገጽ ላይ በማንና እንዴት እንደወጣ ማጣራት እየተደረገ መሆኑን ቃል አቀባዩ ጠቅሰዋል።
በተፈጠረው ክስተት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተሰማውን ጸጸት ገልጸው ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ ጠይቀዋል።
መረጃው እንደደረሰ ካርታውን ከሚኒስቴሩ ድረ ገጽ በፍጥነት በማውረድ የማስተካከያ መግለጫ እንዲወጣ መደረጉን አብራርተዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ግንቦት 17 ቀን የተከበረውን የአፍሪካ ቀንን አስመልክቶ በጻፈው ጹሁፍ ላይ በተጠቀመው የአፍሪካ ካርታ ነው ስህተቱ የተፈጠረው።