ፓርቲው ኅብረ-ብሄራዊት አገር ለመገንባትና አገራዊው ለውጥን ከሚያራምዱ ፓርቲዎች ለመጣመር ፍላጎት አለኝ አለ - ኢዜአ አማርኛ
ፓርቲው ኅብረ-ብሄራዊት አገር ለመገንባትና አገራዊው ለውጥን ከሚያራምዱ ፓርቲዎች ለመጣመር ፍላጎት አለኝ አለ
ሶዶግንቦት 20/2011 የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ)ኅብረ-ብሄራዊት አገር ለመገንባትና አገራዊው ለውጥን ለማራመድ ከሚሰሩ ፓርቲዎች ለመጣመር እንደሚፈልግ ገለጸ።
የፓርቲዉ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ በወላይታ ሶዶ ከተማ በተካሄደ ስብሰባ ላይ እንደተናገሩት ፓርቲያቸው ነጻትና ፍትህ የሰፈነባት ለዜጎቿ ደህንነት ምቹ አገር ለመገንባት ከሚፈልግ ፓርቲና ግለሰብ ጋር ለመስራት ዝግጁ ነው።
በፓርቲዎች መካከል የሚታየው መጠላለፍና ተከባብሮ ያለመስራት ለተፎካካሪነት ፈተና ከመሆን ባለፈ፤ ሕዝብም ተስፋ እንዲቆርጥ እያደረገ ነው ያሉት አቶ ተሻለ፣ ከግለኝነትና አንዱ በሌላው መክሰም ከመበልጸግ አመለካከት በመውጣት ለዜጎችና ለአገር ጉዳይ ቅድሚያ መስጠት ይገባል ብለዋል።
በአገሪቱ የተጀመረው የለውጥ ሂደት ውጤታማ እንዲሆን የተረጋጋና የሰከነ መንፈስ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል፡፡
በአገሪቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን ከመሠረቱ ለመንቀል ፓርቲያቸው አማራጮችን ይዞ መቅረቡንም አቶ ተሻለ አስታውቀዋል፡፡
ፓርቲው ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰ ስብዕና ያለው፣ከብሄርተኝነትና ጠባብነት የተላቀቀ አስተሳሰብ ያላቸው ዜጎች ለማውጣት እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ዶክተር ክብረት ዓለማየሁ ናቸው፡፡
ዜጎች በኅብረ-ብሄራዊነቷ ለዓለም ምሳሌ ሆና በኖረችው አገር እየተስተዋለ ያለውን ስጋት ከደቀኑ አፍራሽ ሁኔታዎች ለማላቀቅ ፓርቲው አማራጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ፓርው በዜጎች መካከል በተፈጠሩ አድሏዊ አሰራሮች ምክንያት እየተፈጠሩ ያሉ አለመግባባቶችና ቅራኔዎችን ለማስወገድ እንደሚታገልም ዶክተር ክብረት አስታውቀዋል፡፡
ወጣቱ ገዢዎች የተበላሹ ታሪኮችን ብቻ በማሳየት የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት የፈጠሩበትን ኢትዮጵያዊነትን የማይወክል ዕይታ ለመለወጥ እንዲተጋ ጠይቀዋል።
የጋሞ ዞን የፓርቲው ተወካይ አቶ ሰለሞን ሳዴ ፓርቲው ሲታገልለት የነበረው ለውጥ ውጤታማ እንዲሆን ብሄራዊ መግባባትና ሠላምን ማስፈን ይገባል ብለዋል፡፡
በስብሰባው በከተማዋና አካባቢዋ የሚገኙ የፓርቲው አመራር፣አባላትና ደጋፊዎች ተሳትፈዋል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ ከ100 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተወሰኑት ወደ ውህደት በመግባት ላይ ናቸው።
በቅርቡም የኢትዮጵያ ዜግነት ለማህበራዊ(ኢዜማ)ና ኅብር የተባሉ ጥምረቶች ተመስርተዋል።