ዩኒቨርሲቲው ከስደት የተመለሱ የምስራቅ ሐረርጌ ነዋሪዎችን መልሶ የሚያቋቁምበትን ፕሮጀክት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው ከስደት የተመለሱ የምስራቅ ሐረርጌ ነዋሪዎችን መልሶ የሚያቋቁምበትን ፕሮጀክት ጀመረ
ድሬዳዋግንቦት 19/2011 የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከስደት የተመለሱ የምስራቅ ሐረርጌ ነዋሪዎችን መልሶ የሚያቋቁምበትን ፕሮጀክት በ290 ሺህ ዩሮ መተግበር ጀመረ።
በአውሮፓ ኅብረት የገንዘብ ድጋፍና በዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት የሚከናወነው ትግበራ ኮሚቴ አባል ዶክተር ከተማ በቀለ ፕሮጀክቱ እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ በፍላጎታቸው ከስደት የተመለሱትንና በዞኑ 15 ወረዳዎች የሚገኙ 259 ስደተኞች ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡
ፕሮጀከቱ ከአፍሪካ ቀንድ አገሮች የተመለሱትን ስደተኞች አእምራዊ ፣ ሥነ-ልቡናዊና ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮቻቸውንና ፍላጎታቸው ላይ በመመስረት የሚከናወን ከመሆኑም በላይ፤ ከኅብረተሰቡ ጋር የነበራቸውን ሁለንተናዊ መስተጋብር የሚያስቀጥሉ ተግባራትም ይከናወኑበታል።
ለአንድ ዓመት የሚተገበረው ፕሮጀክት ውጤታማ እንዲሆን የተቀናጀ እንቅስቃሴ ይደረጋል ብለዋል፡፡
''ፕሮጀክቱ በተመላሾቹ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ያደርጋል። በመረጡት አዋጭ የሥራ መስክ ስልጠናና ድጋፍ ይሰጣል።ለስራቸው ማንቀሳቀሻ እንደመረጡት የሥራ መስክበዓይነት ድጋፍ ያደርግላቸዋል፤ በዘላቂነት መቋቋማቸውም ይፈተሻል፤ ይገመገማል'' ብለዋል፡፡
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደራዊና የተማሪዎች ጉዳይ ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጀይላን ወልይ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የተመላሾችን ሥነ-ልቡናዊ፤ ስሜታዊ፣ ሞራላዊና ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
''እነዚህ ላይ የሚሰሩ ተግባራት በአገር ሰርቶ የመለወጥን እምነት ከማፅናት በላይ፤ ለስደት የተዘጋጁትም እግራቸውን እንዲሰበስቡ ያግዛል''ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ሌሎች ተመላሾች ከኅብረተሰቡ ጋር የሚቀላቀሉበትን ሁኔታ እንዲፈጥር ፕሮፌሰር ጀይላን ጠይቀዋል፡፡
የምስራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳደርተወካይ አቶ መስፍን ጌታቸው ፍልሰት በሚበዛበት ዞን ፕሮጀክቱ መተግበሩ ለአካባቢው ነዋሪዎች ተስፋ ሰጪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለፕሮጀክቱ ስኬታማነትም ከዞን እስከ ቀበሌ ያሉ አመራሮች የተቀናጀ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አቶ መስፍን አረጋግጠዋል።
የአለም አቀፍ የፍሰት ድርጅት የኢትዮጵያ የፕሮግራም አስተባባሪ ወይዘሪት ሳራ ባሻ ድርጅቱ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ስደት በሚበዛባቸው ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ከስደት በፈቃዳቸው የተመለሱ ከ5ሺህ በላይ ስደተኞችን መልሶ እያቋቋመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዞኑ የሚተገበረው ፕሮጀከት በአገሪቱ ለሶስት ዓመታት በሚተገበረው ፕሮጀክት አካል መሆኑንም አስረድተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ፕሮጀክቱን ከመተግበር በተጓዳኝ በስደትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ መፍትሄ አመላካች ጥናቶችን እንዲያከናውንም ጠይቀዋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት በመደበው 43 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ በኢትዮጵያ ፣በሱዳን ፣ በጅቡቲና በሶማሊያ ከስደት ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም እየሰራ መሆኑ በዚሁ ወቅት ተገልጿል፡፡