ኤች አይ ቪን ለመከላከል ህብረተሰቡን በማስተማር የድርሻችንን እንወጣለን… በምስራቅ አማራ የሃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
ኤች አይ ቪን ለመከላከል ህብረተሰቡን በማስተማር የድርሻችንን እንወጣለን… በምስራቅ አማራ የሃይማኖት አባቶች
ግንቦት 20/2011 በአማራ ክልል የኤች አይ.ቪ.ኤድስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሃይማኖት አባቶች ህብረተሰቡን በማስተማር የድርሻቸውን እንደሚወጡ የምስራቅ አማራ የሃይማኖት አባቶች ገለጹ።
የሃይማኖት አባቶቹ የጸረ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መድኃኒትን ከፀበል ጋር አብሮ መውሰድ እንደሚቻል ህብረተሰቡን የማስገንዘብ ሥራ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
የጸረ ኤች አይ ቪኤድስ መድኃኒት ከፀበል ጋር በሚኖረው አንድነት ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ ተካሂዷል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ባዘጋጀው በእዚህ መድረክ ላይ ከምስራቅ አማራ ዞኖች የተውጣጡ ከ200 በላይ የሃይማኖት አባቶች ተሳትፈዋል።
ከደቡብ ወሎ ዞን አልቡኮ ወረዳ የመጡት የመድረኩ ተሳታፊ ቄስ አወቀ ከተማ እንደገለጹት የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሃይማኖት አባቶችና መንግስት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል።
በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ባለው የበሽታው ስርጭት መጠን መደናገጣቸውን ገልጸው፣ በቀጣይ ወደመጡበት የእምነት ተቋም ሲመለሱ ከዚህ በፊት ስለበሽታው ይሰጡት የነበረውን ትምህርት በማጠናከር ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የጸረ ኤች አይ ቪ መድኃኒትን ከፀበል ጋር አጣጥሞ ቢወሰድ እምነቱ እንደማይከለክል ገልጸው ለእምነቱ ተከታዮች ይህንን በማስገንዘብ በሽታውን ለመከላከል የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ አመልክተዋል።
የዋግምራ ብሔረሰብ ዞን ሀገረስብከት የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊመጋቢ አዲስ ተመስገን መዘምር በበኩላቸው “መድኃኒቱም ሆነ ፀበል ከእግዝአቢሔር የተሰጠ ፀጋ በመሆኑ ሁሙማን አጣጥመው ቢወስዱት አይቃረንም” ብለዋል።
የቃሉ ወረዳ እስልምና ሃይማኖትን ወክለው የመጡት አቶ ይማም ሀሰን እንደተናገሩት በአካባቢው ያለውን ፍል ውሃ የሚጠቀሙ ፀበልተኞችን ከመንከባከብና ከመደገፍ ጎን ለጎን ስለ መድኃኒቱ አጠቃቀምና አስፈላጊነት እያስተማሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በእዚህም በአካባቢው የሚኖሩ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ወገኖች ቀደም ሲል የነበራቸውን አስተሳሰብ ትተው መድኃኒታቸውን ከጸበል ጋር አጣጥመው መውሰድ እንደጀመሩ ተናግረዋል።
“በህክምና ባለሙያ የታዘዘን ማንኛውንም አይነት መድኃኒት ህሙማን እንዳይወስዱ የሚከለክል ቀኖና በእምነቱ የለም” ያሉት ደግሞ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከሚዳ ወረዳ የመጡት መሪጌታ ቸሩ መርሻ ናቸው።
በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የኤች አይቪ ኤድስ ዘርፈ ብዙ ምላሽ የዕቅድ ግምገማ ባለሙያ አቶ መንግስቱ መንገሻ በኩላቸው እንደገለጹት የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2016 ይፋ ባደረገው ጥናት በሀገሪቱ ከ606 ሺህ በላይ ሰዎች ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 30 ከመቶ የሚሆኑት በአማራ ክልል የሚገኙ ናቸው።
አቶ መንግስቱ እንዳሉት በተያዘው ዓመት ዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ በክልሉ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሰዎች ነጻ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ምርመራ አድርገው ከ10ሺህ በላይ ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው ተገኝቶባቸዋል።
ቫይረሱ በደማቸው ካለባቸው ሰዎች መካከልም ከ7 ሺህ በላይ ሰዎች መድኃኒቱን መውሰድ እንደጀመሩ ገልጸው፣ መድኃኒት መውሰድ ያልጀመሩ ሌሎች ከ5 ሺህ በላይ የሚጠጉ ሰዎች በፀበል አካባቢ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ የተሳተፉ ፀበል አጥማቂዎችና ወንጌል ሰባኪያንን ግንዛቤ በማሳደግና በማስተማር በቀጣይ ህሙማንን አሳምነው መድኃኒት እንዲጀምሩ ለማድረግ ሲባል መድረኩ መዘጋጀቱንም አስረድተዋል።
አቶ መንግስቱ እንዳሉት በአማራ ክልል በተደረገ የናሙና ጥናት መሰረት እስካሁን ድረስ በክልሉ ከ184 ሺህ በላይ ሰዎች ከቫይረሱ ጋር ይኖራሉ።
ከእነዚህ ውስጥ የፀረ ኤች አይ ቪኤድስ መድኃኒት እየወሰዱ ያሉት 141ሺህ ሰዎች ብቻ መሆናቸውን ታውቋል።